
ሰቆጣ፡ ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ከ2017ዓ.ም ጀምሮ የሦስተኛ ወገን እና የተርጋ ቁጥር አገልግሎት መሥጠት ጀምሯል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከኾኑት መካከል የሦስት እግር አሽከርካሪው ዘውዱ ማረው አዳዲስ ተሽከርካሪ ለማስገባት በቅርበት የሦስተኛ ወገን እና የተርጋ ቁጥር አገልግሎት በሰቆጣ ከተማ መጀመሩ ከተጨማሪ ወጪ እንዲተርፉ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። ይህም ለማኅበረሰቡም ፈጣን አገልግሎት እንዲሰጡ እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አስፋው አዛኔ የተሽከርካሪ የሦስተኛ ወገን ቦሎ አገልግሎት፣ የብቃት ማረጋገጫ እና የታርጋ ቁጥር አገልግሎት በዞናችን መጀመሩ ከአላስፈላጊ እንግልት እና ወጪ ነጻ አድርጎናል ብለዋል።
ከአሁን በፊት ተሽከርካሪ ተጭኖ ባሕር ዳር፣ ወልድያ እና መቀሌ ድረስ በመውሰድ የታርጋ ቁጥር እንዲያገኝ ይደረግ ነበር ብለዋል። አቶ አስፋው ወረፋ ሲኾን እስከ ሳምንት ድረስ ለመቆየት እንገደድ ነበር ነው ያሉት።
ለዓመታት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ የነበረውን የሦስተኛ ወገን አገልግሎት፣ የታርጋ ቁጥር እና የብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት መፈቀዱ ለዓመታት የቆየውን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ በመመለስ አገልግሎቱን በጥራት እየሰጡ እንደሚገኙ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትራንስፖርት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዘውዱ የኋላው ገልጸዋል።
በተያዘው ዓመትም 248 ተሸክርካሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ መቻላቸውን የገለጹት ኀላፊው የላይሰንስ መረጃቸው በአጎራባች ከተሞች እና ክልሎች የነበሩ ከ80 በላይ የሚኾኑ የተሽከርካሪ መረጃዎችን ወደ ዞኑ ማዛወር መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ በሠራው የተጠናከረ የአገልግሎት አሰጣጥ ተግባር የትራፊክ አደጋውን ከመቀነስ ባሻገር የትራንስፖርት አገልግሎቱ በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
በቀጣይ ዓመትም ፈጣን አገልግሎት በመሥጠት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን አቅደው ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን