
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
በአፈጻጸም ሪፖርታቸውም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የንግድ ምዝገባ፣ የፈቃድ መስጠት እና እድሳት አገልግሎትን ማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል። የኦንላይን አገልግሎት መስጫ ማዕከሎችን በማጠናከር 527 ሺህ 170 አገልግሎቶችን በኦንላይ መስጠት እንደተቻለ ተናግረዋል።
1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በመመደብ አምራች እና ሸማቹን የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው ብለዋል። በስምንቱ ሪጂኦፖሊታንት ከተሞች እየተገነቡ የሚገኙ የገበያ ማዕከላት ግንባታቸው እየተጠናቀቀ መኾኑንም ተናግረዋል።
የገበያ ማዕከላት ግንባታዎቹ በወረዳ እና በከተሞች ላይም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት። የገበያ ማዕከላት የግብይት ሰንሰሉትን በማሳጠር ዋጋን በማረጋጋት ፋይዳቸው የጎላ ነው ብለዋል። ጅምሩን ማስፋት እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሰብል እና የኢንዱስትሪ ምርትን ትስስር በማጠናከር 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማስተሳሰር ተችሏል ነው ያሉት። 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ለምርት ግዥ ጥቅም ላይ ማዋል እንደተቻለም አንስተዋል።
140 ንግድ እና ባዛሮችን በማዘጋጀት 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና እና የኢንደስትሪ ምርት፣ 18 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና ፋሳሽ ሳሙና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። ይህም የኑሮ ውድነቱ ይፈጥር የነበረውን ተጽዕኖ መቀነስ ችሏል ብለዋል።
6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 625 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት። በዓሳ ምርት፣ በዳልጋ ከብት፣ በበግ እና ፍየል በመላክ ከእንስሳት ውጤቶች ከ2 ነጥብ 455 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።
ክልሉ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ እያሳደጉ መሄድ እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!