
ጎንደር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሕንፃዎቹ ስምንት የመማሪያ ክፍሎችን የያዙ ሲኾኑ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገባቸው የጎንደር አካባቢ አልማ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር ደረጀ ዘውዴ ተናግረዋል።
ተቋማቸው በበጀት ዓመቱ 160 ሚሊዮን ብር ከአባላቱ መሰብሰቡን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ በ2017 ዓ.ም 40 መማሪያ ክፍሎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ቀሪ 102 የመማሪያ ክፍሎችን ደግሞ እስከ ነሐሴ መጨረሻ እንደሚጠናቀቁ አንስተዋል።
በባለፉት አምስት ዓመታት በለውጥ እቅዱ 148 ፕሮጀክቶችን ማከናወን መቻሉንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል። በመኾኑም 441 ሺህ 877 የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ያስረዱት። አልማ በሠራቸው ፕሮጀክቶች ከ39 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩንም ዳይሬክተሩ አብራራተዋል።
አልማ ከመደበኛ አባላት ባሻገር ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ግንባታዎች፣ ሥልጠናዎች፣ ለትምህርት ቤቶች እና ለጤና ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ለትምህርት እና ለጤና ተቋማት የቁሳቁስ ድጋፍ በተቋሙ ከ102 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መኾኑም ተገልጿል።
ዛሬ ከተመረቁት በተጨማሪ አልማ በታች አርማጭሆ ወረዳ 10 መማሪያ ክፍሎችን የያዘ ባለ አንድ ፎቅ የመማሪያ ክፍል እየተሠራ መኾኑ ተጠቅሷል። በሳንጃ ከተማ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ መቀመጡም ተጠቅሷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የታች አርማጭሆ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አስማረ የኋላሸት አልማ በወረዳው በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች እየሠራ ያለው ተግባር የሚበረታታ ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ የተመረቁ የመማሪያ ክፍሎች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው አንስተዋል።
በዞኑ እየተሠሩ ያሉ የአልማ ፕሮጀክቶችን ለማብዛት የአባላትን ቁጥር መጨመር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና መሬት መምሪያ ኀላፊ አላምረው አበራ ናቸው።
የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው የጊዜ መርሐ ግብር ለማጠናቀቅ ሰላም ቀዳሚ ተግባር በመኾኑ ማኅበረሰቡ ለዘላቂ ሰላም እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ :- አዲስ ዓለማየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!