
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አቢሲኒያ ባንክ በመላው ሀገሪቱ ባሉ ቅርንጫፎቹ ተግባራዊ የሚደረግ ከወረቀት ነጻ የባንክ አገልግሎትን አስጀምሯል፡፡
እንደ አውሮፖውያኑ አቆጣጠር በ1996 የተመሠረተው የአቢሲኒያ ባንክ በየጊዜው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የባንኩን አገልግሎት የሚያሻሽሉ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡
ባንኩ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 928 ቅርንጫፎቹ 24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚችል ከወረቀት ነጻ የባንክ አገልግሎትን ለደንበኞቹ ማቅረቡን የባንኩ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ በቃሉ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ይፋ ያደረገው ከወረቀት ነጻ የባንክ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ዲጂታል ፍኖተ ካርታ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ መኾኑን ገልጸዋል። ባንኩ ሀገራዊ አበርክቶውን ለማሳደግም እንደሚሠራ ነው የጠቆሙት፡፡
ባንኩ ይፋ ያደረገው ከወረቀት ነጻ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት በስድስት ቋንቋዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እሰመለዓለም ምህረቱ አቢሲኒያ ባንክ በፍይናንሱ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ አለው ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ በቴክኖሎጂ የታገዘ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል ጥረት እያደረገ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው የፋይናንስ ዘርፉ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ እንዲኾን ደንበኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የባንክ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን