“የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሕዝባችን የሕልውና ጉዳይ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

13

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸምን አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም በክልሉ ባልተለመደ ኹኔታ የሕግ የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱን ተናግረዋል። የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት የሕልውና አደጋ ላይ የወደቀበትን ጊዜ እንዳሳለፈም ገልጸዋል።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሕዝቡ ሰላም ተናግቶ መደበኛ ሥራውን እንዳይሠራ እና ሕይወቱን እንዳይመራ በታጣቂ ቡድኖች ግፍ እና በደል ደርሶበታል ነው ያሉት።

የክልሉ ሕዝብ የተሸረበውን ሴራ እና የጽንፈኝነት አስተሳሰብ በተባበረ ክንድ ማክሸፉንም አንስተዋል። የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ ኀይሎች በሠሩት ሥራ የክልሉ ሰላም በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን ገልጸዋል።

የጽንፈኛ ኀይሉ የሎጂስቲክ እና የሰው ኀይሉ ተዳክሞ ሕይወቱን ለማሰንበት በየጎሬው እየተሹለከለከ መኾኑንም ተናግረዋል። የሰላም ማስከበር እና የመልሶ ግንባታ ሥራውን የበለጠ እያጠናከሩ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም መመለስ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

ሰላምን የማረጋገጥ እና የማጽናት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ፣ ከጠመንጃ ይልቅ በሀሳብ የበላይነት በማመን ሰላምን እንዲመርጡ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የክልሉ ሕዝብ በአደባባይ ወጥቶ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር፣ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር መጠየቁንም አንስተዋል።

“የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሕዝባችን የሕልውና ጉዳይ ነው” ብለዋል። በአንድ በኩል ዘወትር የማይታጠፈውን የሰላም ጥሪ እናቀርባለን፣ ለሰላም አማራጭ ተገዥ የማይኾኑትን ደግሞ ሕግ በማስከበር የመንግሥት ሚናችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።

የሲቪል ሰርቪስ አሥተዳደሩን ለማጠናከር የመንግሥት ሠራተኞችን አቅም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ከሰላም ማስከበሩ ጎን ለጎን ዜጎች በመንግሥት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ መሠራቱንም አንስተዋል።

የመንግሥት ተቋማት ለኅብረተሰቡ መስጠት ያለባቸውን አገልግሎት በጥራት እና በውጤታማነት እንዲሰጡ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል። የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ሪፎርም ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል።

ክልሉ ሪፎርሙን ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ፣ ስትራቴጂዎች፣ ጥናቶችን እና ልዩ ልዩ የአሠራር ማንዋሎችን እያዘጋጀ መኾኑን አስታውቀዋል። ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የሲቪል ሰርቪስን ማዘመን ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት ለነገ የማይባል ተግባር እንደኾነም አንስተዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ጠንካራ ዕቅድ አቅደው መሥራታቸውን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ ክልሉ የጸጥታ ችግር የከረመበት በማይመስል መልኩ በርካታ ውጤቶች እንደተገኙ ነው የተናገሩት።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ እና ሌሎች ሚዲያዎች በክልሉ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅዱ እንዲሳካ ሠፊ ሥራ ሠርተዋል ነው ያሉት።

ለ2018 በጀት ዓመት የላቀ ሥራ ለመሥራት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል ነው ያሉት። የ2017 በጀት ዓመት በችግርም ውስጥ ኾነን በእልህ እና በቁጭት ከሰላሙ ጊዜ ያልተናነሰ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል የተማርንበት ነው ብለዋል።

ጠንካራ ሥራዎች በአዲሱ በጀት ዓመት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየሠራን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል” የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
Next articleየፋይናንስ ዘርፉ ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ እንዲኾን ደንበኞች ላይ ትኩረት ያደረገ የባንክ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል።