
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በጀመረቻቸው ጥረቶች በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል፤ ለላቀ ስኬትም ጥረቶች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ከጣልያን መንግሥት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመቀናጀት ሁለተኛውን የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ እንድታዘጋጅ ተመርጣለች፡፡ ይህም በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለውን ሚና የሚጎላ፣ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የጀመረቻቸውን ስኬታማ ተግባራት የሚያበረታታ ነው፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት በመጀመሪያው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ በምታስተናግደው መድረክ ይገመገማል፤ ቀጣይ አቅጣጫዎችም ይቀመጣሉ፡፡
ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ጉባኤ ርሃብን ስለማስወገድ እና ምግብ ዋስትና፣ ስለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶች ምክክር ይደረጋል፤ ቀጣይ መወሰድ የሚገባቸው ርምጃዎችም ይመላከታሉ፡፡
ኢትዮጵያ ጉባኤውን የምታስተናግደው ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን በማስመዝገብ የማንሰራራት ጉዞን በጀመረችበት ወቅት ነው፡፡ ለጉባኤው በተሞክሮነት የምታካፍላቸው በርካታ ስኬቶችም አሏት፡፡
በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በለማት ትሩፋት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ ስኬታማ ድሎችን አስመዝግባለች፡፡ በአየር ንብረት ለውጥ ረገድም ባለፉት በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ለዓለም አብነት ናት፡፡
ጉባኤው በሚካሄድበት በዚህ ክረምትም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየተጋች ነው፡፡ የሚተከሉት ችግኞች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻላቸውም በላይ የምግብ ዋስትናን እና ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ሚና ያላቸው ናቸው፡፡
የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤን እንድታስተናግድ ለኢትዮጵያ ዕድል መሰጠቱም ይህንን ጅምር ዕውቅና የሚሰጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለብዝኅ ዘርፍ ኢኮኖሚ እየገነባች እና ሁለንተናዊ ስኬት እያስመዘገበች ባለችበት በዚህ ወቅት ከሐምሌ 20 እስከ 22/2017 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ሥርዓት ጉባኤን በአዲስ አበባ ታስተናግዳለች፡፡
በጉባኤው የሀገር መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ የምግብ አምራቾች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሴቶች ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም የመዲናዋን ገጽታ በእጅጉ ለውጣ እንግዶችን በላቀ ዝግጅት ለመቀበል ተሰናድታለች፡፡ በርካታ ስኬቶቿንም በልምድነት ለማካፈል ተዘጋጅታለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ለዘመናት ያስቀጠሉትን ሁለትዮሽ እና ባሉበዝኅ ወገን ግንኙነት ትኩረት የመስጠት ልምድ ተጠቅመው ጉባኤውን በላቀ ስኬት ለማስተናገድ በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!