
ጎንደር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ የሚገኘው የጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዲፕሎማ የጤና ዘርፍ ሲያስተምራቸው የቆዩ 571 ተማሪዎችን ነው ዛሬ ያስመረቀው።
ተመራቂዎቹ በነርሲንግ፣ በፋርማሲ ቴክኒሽያን፣ በሜዲካል ላብራቶሪ፣ በሚድ ዋይፈሪ እና በጤና መረጃ ቴክኒሽያን አምስት የትምህርት ዘርፍ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መኾናቸውንም የኮሌጁ ዲን ዘመነ ሀብቱ ተናግረዋል።
ኮሌጁ 20ኛውን የምረቃ መርሐ ግብሩን ማካሄዱን የገለጹት አቶ ዘመነ የዘንድሮው ተመራቂዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መኾናቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ለተመራቂዎች እና ለቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ተመራቂዎቹ በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን እውቀት በመተግበር በቀጣይ የሙያ የተግባር ምዕራፋቸው ማኅበረሰቡን በቀናነት እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጤና ሙያ ሰብዓዊነትን የሚጠይቅ መኾኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባዋ ተመራቂዎች በሠለጠኑበት ሙያ ከማገልገል ባለፈ ችግር ፈች ምርምሮችን በማካሄድ ማኅበረሰቡን እንዲያግዙ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ መልካሙ ጌትነት በበኩላቸው የጤና ሙያ ክብር የኾነውን የሰው ልጅ ሕይዎት ለመጠበቅ ለጤና ባለሙያዎች በአደራነት የሚሰጥ መኾኑን አንስተው ተመራቂዎቹ ሙያዊ መርሕን መሰረት በማድረግ በሚሰማሩባቸው የሙያ መስክ ሁሉ ማኅበረሰቡን በገቡት ቃል መሰረት በማገልገል ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ መልካሙ የክልሉ መንግሥት የጤና አገልግሎትን ለመስጠት በሚያደርገው ጥረት የጠዳ ሳይንስ ኮሌጅ የበኩሉን ተቋማዊ ኀላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ኮሌጁ የተሻለ የጤና ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያደርገው ጉዞ ስኬታማ እንዲኾን የክልሉ ጤና ቢሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎችም በበኩላቸው በኮሌጅ ቆይታቸው ያገኙትን የፅንሰ ሀሳብ እና የተግባር እውቀት ተጠቅመው ማኅበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
በምረቃ ግብሩ አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በ1997 ዓ.ም መደበኛ ሥራውን የጀመረ ጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጤናው ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል። በዲፕሎማ የጤና ዘርፍ ሲያበረክተው ከነበረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ በአኹኑ ወቅትም በጤናው ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ተማሪዎቹን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል።
ዘጋቢ:- ሀይሉ ማሞ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!