“የመካከለኛው ዘመን ቅርሶችን ለመጠገን የሚረዳ የኖራ ፋብሪካ በግንባታ ላይ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

7

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው። የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እያቀረቡ ነው።

በሪፖርታቸውም በበጀት ዓመቱ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤን ለማሳደግ ከመንግሥት 59 ነጥብ 45 ሚሊዮን እና ከማኅበረሰቡ በጀት ፈሰስ በማድረግ በአጠቃላይ በ80 ሚሊዮን ብር የቅርስ ጥበቃ እና ክብካቤ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

156 ቋሚ እና 604 ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን ማደስ ተችሏል ብለዋል። በኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ቅርሶችን ለመጠገን የሚረዳ የኖራ ጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ የኖራ ግንባታ ፋብሪካ በሂደት ላይ መኾኑን ተናግረዋል።

ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ክልሉን ከከፍተኛ ወጪ እና ውጣ ውረድ እንደሚያድን ገልጸዋል። የቅርስ ጥገና አቅርቦትን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል። የተንቀሳቃሽ ቅርሶችን አያያዝ ለማሳደግ 58 ሙዚየሞችን ማጠናከር እንደተቻለም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሙዚየም ግንባታ እና የውጫሌ ይስማ ንጉሥ ሙዚየም የማደራጀት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የደሴ ሙዚየም የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ሥራ መሠራቱን ነው የተናገሩት። ባሕላዊ እሴቶችን ለማጠናከር እና የቱሪዝም ገበያ ለማድረግ መሠራቱንም ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በ107 የመስህብ ሥፍራዎች 259 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ፣ በ69 የመስህብ ስፍራዎች የመጸዳጃ ቤት ግንባታ፣ የመታጠቢያ ግንባታዎች፣ በ21 የመስህብ ስፍራዎች የመብራት አቅርቦት፣ በ23 መስህብ ስፍራዎች የመጠለያ ግንባታ እና በ37 የመስህብ ሥፍራዎች የገጸ ምድር ማስዋብ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 24 ሺህ 415 የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ክልሉን እንደጎበኙት ገልጸዋል። ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፣ ከውጭ ሀገር ጎብኝዎች 155 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት።

የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክ አገልግሎትን ፈጣን እና ቀልጣፋ ለማድረግ መሠራቱንም ተናግረዋል። የትራንስፖርት አገልግሎትን የተሳለጠ ለማድረግ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ መሠራቱን ነው የተናገሩት።

መናኸሪያዎችን ከእንግልት እና ከወከባ ለማውጣት የኢ-ቲኬቲንግ ሥራ ተጀምሯል ነው ያሉት። ይህም የኅብረተሰቡን እንግልት ቀንሷል ብለዋል። አሁንም ማዘመን እና ተጨማሪ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትምህርት የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል አስፈላጊ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next articleየጠዳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡