
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2017 (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
በሪፖርታቸውም የክልሉ መንግሥት የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት ግን ክፍተቶች እንዳሉ ነው የገለጹት። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የትምህርት ዘርፉን እንደጎዳው ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ 4 ሺህ 279 የመማርያ ክፍሎችን መገንባት እንደተቻለ ገልጸዋል። 12 ሺህ 647 ክፍሎች መጠገናቸውንም አስታውቀዋል። 19 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍት በክልሉ፣ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን መጻሕፍት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር ታትመው ሁሉንም ማሠራጨት እንደተቻለ ተናግረዋል። በሥርጭት ሂደቱ ፈታኝ ችግሮች እንደነበሩም አስታውዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ከ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ለመመዝገብ ታቅዶ በሦስት ዙር መመዝገብ የተቻለው 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ ነው ብለዋል።
4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች እኩይ ዓላማ ባላቸው ኃይሎች ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። ትምህርት በፈተና ውስጥ መኾኑንም አመላክተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ መጎዳታቸውንም ገልጸዋል።
የገጠመው ጉዳት ከደረጃ በታች ለነበሩ ትምህርት ቤቶች ሌላ ፈተና እንደኾነ ነው ያሰኑት። የትምህርት ሥርዓቱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የትምህርት ተደራሽነት፣ ጥራት፣ ተገቢነት ማረጋገጥ፣ የትምህርት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ግብዓትን ማሟላት፣ መሠረተ ልማትን ማሻሻል እንደሚገባ አንስተዋል።
ትምህርት የማንኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣሪያ እንዳይኾን መሥራት የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል አስፈላጊ ነው ብለዋል። የተማሪዎች ምገባ በትኩረት ሊሠራበት የሚገባ እንደኾነም አንስተዋል። የትምህርት ዘርፉን ከገጠመው ችግር ለማውጣት ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።
በአዲሱ በጀት ዓመት በትምህርት ዘርፉ የተቃጣው አስነዋሪ ድርጊት እንዲቆም መሥራት እንደሚገባም ገልጸዋል። በትምህርት ትውልድን የማነጽ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ይገባል ብለዋል። በትምህርት ዘርፉ የገጠመውን ችግር መፍታት ካልተቻለ መወዳደር እንደማይቻልም አመላክተዋል።
የክልሉ መንግሥት በተለየ ትኩረት ከሚመለከታቸው ተቋማት መካከል ጤና አንደኛው መኾኑም ገልጸዋል። የጤናው ዘርፍ በችግርም ውስጥ ኾኖ የተሻለ ሥራ እና ውጤት የታየበት ነው ብለዋል። ድንገተኛ አደጋዎች እና ወረርሽኞችን ለመከላከል መሠራቱን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባዋራ እና እማውራዎችን የጤና መድኅን አባል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራት እና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ አዳዲስ አሠራሮች እየተተገበሩ ነው ብለዋል።
በሕጻናት የጤና አገልግሎት እና በእናቶች ጤናም ትኩረት ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!