“ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ለኾነው ግብርና ትኩረት መስጠት ይገባል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

13

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ነው።

በሪፖርታቸውም የክልሉ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ግብርና መኾኑን ተናግረዋል። ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ለኾነው ግብርና ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል። በ2017 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 170 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ነው ያሉት።

ምርቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ መሰራጨቱንም አስታውሰዋል። ለበጋ ስንዴ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሠራም ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱንም አንስተዋል።

በ2017/18 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ለማሠራጨት ታቅዶ ግዥ መፈጸሙን ገልጸዋል።

5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ተናግረዋል። የክልሉ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ እንዲከተሉ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ሥራም ጥሩ ሥራ መሠራቱን ነው የገለጹት።

የእንስሳት ሃብት በክልሉ ከሰብል ልማት ቀጥሎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በወተት፣ በስጋ፣ በእንቁላል፣ በማር ምርት ጥሩ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን ለማጠናከር መሠራቱንም ገልጸዋል።

የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ መሠራቱንም ተናግረዋል። በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖች ድጋፍ መደረጉንም ገልጸዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበጀት ዓመቱ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ግማሽ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እየሠራ ነው።
Next article“ትምህርት የትውልድ ቅብብሎሽን ለማስቀጠል አስፈላጊ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ