
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
በሪፖርታቸውም 2 ሺህ 465 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተዋል ብለዋል። አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዘጠኝ በመቶ ማደጉንም ገልጸዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ቁጥር ከባለፈው ዓመት የተሻለ ቢኾንም ከዕቅዱ አንጻር ዝቅተኛ ነው ብለዋል። 3 ሺህ 754 ባለሃብቶች ፈቃዳቸውን ማደሳቸውንም ተናግረዋል።
106 ሺህ 457 ቶን ምርት በመላክ 156 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችሏል ብለዋል።
775 ነጥብ 271 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉንም ገልጸዋል። በርካታ አምራች እንዱስትሪዎችን ወደ ምርት ማስገባት መቻሉንም ተናግረዋል። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 59 ነጥብ 22 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል።
ለማዕድን ሃብት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ለባለሃብቶች የማዕድን ፈቃድ መስጠት መቻሉንም ገልጸዋል።
32 ሺህ 229 ኪሎ ግራም የወርቅ እና የኦፓል ምርት ወደ ውጭ በመላክ 14 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉንም ተናግረዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። 70 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር ከውጭ የሚገባ ምንዛሬን ለማዳን ታቅዶ 113 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የማዕድን ምርትን ማሳደግ እንደተቻለም ገልጸዋል። የማዕድን ፋብሪካዎቹ ድጋፍ እና ክትትል እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን