
ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመንግሥትን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ እያቀረቡ ነው።
በሪፖርታቸውም በ2017 በጀት ዓመት ነባራዊ ሁኔታውን እና የክልሉን አቅም መሠረት ያደረገ ዕቅድ መታቀዱን አስታውሰዋል። በበጀት ዓመቱ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
የክልሉ ሰላም በመሻሻሉ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል። አንዳንድ ሥራዎች የተሟላ ሰላም ቢኖር ምን ያክል ሥራ ሊሠራ እንደሚችል ቁጭት የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ መሥራታቸውንም ተናግረዋል። በክልሉ የማክሮ ኢኮኖሚን ውጤታማ ለማድረግ መሠራቱንም ተናግረዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የክልሉ ጥቅል ምርት 370 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መኾኑንም ገልጸዋል። ስድስት በመቶ እድገት መመዝገቡንም ተናግረዋል። ዘላቂ ልማት ከተረጋገጠ በክልሉ ተስፋ ሰጪ እድገት እንዳለም አንስተዋል።
በክልሉ የዋጋ ንረትን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። የዋጋ ንረት መቀነሱንም ገልጸዋል። ነገር ግን አሁንም በርካታ ሥራዎች መሥራት እንደሚጠበቅ እና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ወገኖችን መታደግ ይገባል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱንም ገልጸዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል ነው ያሉት።
ከ60 ሺህ በላይ የሚኾኑ ወጣቶች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዳገኙም ተናግረዋል። ካለው የሥራ ዕድል ፍላጎት አንጻር አሁንም ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
የመንግሥት ገቢ እና ወጪ ሚዛንን ለመጠበቅ መሠራቱንም ገልጸዋል። የገቢ አሰባሰብ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከባለፈው በጀት ዓመት የበለጠ ገቢ መሰብሰብ መቻሉንም ገልጸዋል። ነገር ግን ክልሉ አሁንም ካለው አቅም አንጻር ገቢን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ትኩረት መሥጠት መቻሉንም ተናግረዋል። በርካታ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ለአዲሱ በጀት ዓመት እርሾ የሚኾኑ ሥራዎችን ሠርተናል ብለዋል። በአዲሱ በጀት ዓመት ጥንካሬዎችን በማጠናከር እና ክፍተቶችን በመሙላት መሥራት እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!