“ዴሞክራሲን ያለ ልማት ማሰብ አይቻልም” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

20

ባሕር ዳር: ሐምሌ 19/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ምክር ቤቶች በሕግ እና በሥርዓት የሚመሩ የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ መኾናቸውን ገልጸዋል።

“ዴሞክራሲን ያለ ልማት ማሰብ አይቻልም ብለዋል” ዋና አፈ ጉባኤዋ። ዴሞክራሲን እና ልማትን አጣጥሞ መሄድ የምክር ቤት አባላት ዋና ተግባር መኾኑንም ገልጸዋል።

የሕዝብ ድምጽ መኾን፣ መንግሥት እና ሕዝብን ማገናኘት፣ መራጩን ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

የክልሉ ምክር ቤት ባለፉት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል። የምክር ቤት አባላት የሕዝብ ድምጽ ኾነዋል፣ ሰላም እንዲረጋገጥ ሠርተዋል፤ አፍራሽ ተግባራትን ታግለዋል ነው ያሉት። የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጨምር እና የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስ መሥራታቸውንም ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት የግል ፍላጎታቸውን ወደ ጎን በመተው የወከላቸውን ሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሠርተዋል ብለዋል።

ውክልናን በአግባቡ ካልተወጣን የሕግ የበላይነት አይረጋገጥም ያሉት አፈ ጉባኤዋ የሕዝብ ውክልናን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አመላክተዋል። ነጻ እና ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማትን ለመገንባት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የፍትሕ ሥርዓቱን ለማዘመን ከ10 በላይ አዋጆች ጸድቀው ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የዳኝነት እና የፍትሕ ተቋማቱን ለማዘመን እንየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የሕዝብ አመኔታን ለማረጋገጥ የፍትሕ ተቋማትን ማዘመን፣ ሙያዊ ሥነ ምግባርን አስቻይ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በ2017 በጀት ዓመት ምክር ቤቱ የመስክ ምልከታ ማድረጉንም ተናግረዋል። በምልከታቸው ተስፋ ሰጪ ተግባራትን መመልከታቸውን አንስተዋል። የአገልግሎት አሠጣጥ እና ሌሎች ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል። በቀጣይ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እና ማሻሻል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ብሔራዊ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ።
Next article“በበጀት ዓመቱ የተሠሩ ሥራዎች ቁጭት የፈጠሩ ናቸው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ