
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሴቶች ማኅበራት ፌዴሬሽን የቦርድ መሪዎች፣ አባል ማኅበራት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የችግኝ ተከላ እና የደም ልገሳ መርሐ ግብር ተካሂደዋል።
የችግኝ ተከላው በባሕር ዳር ከተማ ለፌዴሬሽኑ ሕንፃ መገንቢያ በተሰጠው ቦታ ላይ ነው የተካሄደው።
በመርሐ ግብሩ ለተሳታፊዎች ከባሕር ዳር ደም ባንክ አገልግሎት በባለሙያዎች የደም ልገሳን አስፈላጊነት እና ጥቅሞች ገለፃ ከተደረገ በኋላ ተሳታፊዎች ደም ለግሰዋል።
ደም የለገሱት የፌዴሬሽኑ ምክትል ቦርድ ሠብሣቢ እና የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንፁህ ሽፈራው ደም ሲለግሱ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ መኾኑን ተናግረዋል።
“ደም የሚፈልጉ በርካታ እናቶች ስላሉ ለእነሱ ደም በመስጠቴ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።
”ለእናቶች ቀድመን መድረስ ያለብን ሴቶች ነን” ያሉት ወይዘሮ ንፁህ ሽፈራው ሁሉም የሚችል ሰው ደም ሊለግስ ይገባል ነው ያሉት።
ሌላው ደም ለጋሽ የፌዴሬሽኑ የፋይናንስ ባለሙያ ዐቢይ ወርቁ ”የኔ ደም የሰው ሕይወት የሚያተርፍ ከኾነ መስጠት አያጎድልምና ሁሌም እለግሳለሁ” ብለዋል።
ደም ሲለግሱ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲኾን ከስጦታዎች ሁሉ ደም መስጠት የሰውን ሕይወት የሚታደግ በመኾኑ ሁሉም ሰው ደም ሊለግስ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!