
ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምንም እንኳን እንደሌሎቹ ጓደኞቿ ተሯሩጣ መሥራት የምትችልባቸው እግሯቿ ባይሠሩም ጠንካራ ሞራል፣ ሌሎች እግር ያላቸው ሰዎችን የሚያስንቅ የሥራ ባሕል እና ብልሀትን የታደለች ወጣት ናት በዛብሽ ጎበዜ።
በዛብሽ ጎበዜ የምትሠራው ሥራ ብዙዎቹ አካል ጉዳተኝነቷን እንዲረሱ ያደርጋቸዋል። ብዙ ጊዜ ሰዎች በምትሠራው ሥራ እና አገልግሎት አዝነውላት ሳይኾን በሥራዋ ተደስተው እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደምትጥር ነው የነገረችን።
ይህች ተምሳሌት የምትኾን ወጣት አካል ጉዳተኛ በደረት ላይ የሚያዙ እቃዎች መሸጥ ጀምራ ውጤታማ መኾን የቻለች ቢኾንም የባሕር ዳር ከተማ የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማት ላይ ለአካል ጉዳተኞች ተንቀሳቅሶ ለመሸጥ የሚያግዙ ባለመኾናቸው ሥራውን ለመለወጥ እንደተገደደች ነው የምትናገረው።
የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማት የሚሠሯቸው ሕንጻዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ መኾን አለባቸው ብላለች።
አካል ጉዳተኞች እንደ አካል ጉዳታቸው ክብደት እና ተፈጥሮ የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል ነው ያለችው።
እነዚህን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ከማኀበረሰቡ እኩል ተሳታፊ እና አምራች ዜጋ እንዲኾኑ የሁሉም ሰው ርብርብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍሬሰላም ዘገየ በክልሉ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ እየተሠራ ያለው ሥራ አጥጋቢ አይደለም፤ ነገር ግን የተወሰነ ለውጥ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየታየ ነው ብለዋል።
አራት ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች በክልሉ እንዳሉ የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ አካል ጉዳተኞችን ትቶ የሚሠራ ማንኛውም ሥራ ውጤት ማምጣቱ አጠያያቂ ነው ይላሉ። በሀገርም ኾነ በክልል ደረጃ መመሪያዎች ይወጣሉ፤ ነገር ግን ተግባራዊ እየኾኑ ነው ማለት አይደለም፣ ብዙ ነገሮች ይቀራሉ ብለዋል።
እንደ አስረጅነት የሕንጻ አዋጅ የትኛውም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እና ተደራሽ መኾን አለባቸው እንደሚል ገልጸዋል።
አዋጁ ከወጣ ሰንበትበት ያለ ቢኾንም እድሳት እየተደረገላቸው ያሉ የድሮዎቹም ይሁኑ አዲስ የሚሠሩት የተለየ ነገር አይታይባቸውም ብለዋል።
ሠራን የሚሏቸው አካል ጉዳተኞችን ወደ ሕንጻዎች የሚያስገቡ መግቢያዎች (ራምፕ) ወደ ውስጥ ሲገቡ ወደ ኋላ ገፍትረው የሚጥሉ፣ ከውስጥ ሲወጡ ደግሞ ወደ ፊት አንደርድረው የሚጥሉ እንደኾኑ አስገንዝበዋል።
አሳንስሮችም ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው ብለዋል። ሕጎችን ከማውጣት ባለፈ ተግባር ላይ አልተሠራባቸውም ነው ያሉት።
አሁን ላይ ሕንጻ ለሚገነቡትም ኾነ እድሳት ለሚደረግባቸው ሕንጻዎች መንግሥትም ኾነ ባለሃብቶች ሕጎችን እና መመሪያውን ተከትለው መሥራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
ሕዝብ እና መንግሥትን የሚያገለግሉ ባለሙያዎች አካል ጉዳተኛ ደንበኞችን በማሰብ አገልግሎት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል።
በአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን ዳይሬክተር መንበሩ የወርቅ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ የአንድ መሥሪያ ቤት ጉዳይ አይደለም ብለዋል።
መንግሥትም ኾነ መንግሥታዊ ያልኾኑ አካላት የሚሰጧቸው ሁሉም አገልግሎቶች እና ምርቶች አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ መኾን አለባቸው ነው ያሉት።
ሁሉንም የአካል ጉዳት አይነት ታሳቢ ያደረገ አሠራር መከተል እንደሚገባም አብራርተዋል።
በጤናው፣ በትምህርት፣ በንግዱ፣ በኢንድስትሪው እና በመልካም አሥተዳደር ዘርፍ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ራሱን የቻለ የተቋማትን ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርጉ ተቋማትን የሚያበቃ፣ የሚመዝን እና እስከ ተጠያቂነት የሚያደርስ አሠራር እንዳለውም ጠቁመዋል።
በየዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችም ኾኑ አሥፈጻሚ አካላት የአመለካከት እና የዕውቅና ችግር ስላለ የማስተማር ከፍ ሲልም ተጠያቂነት የማምጣት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ከባለፈው ዓመት በተለየ በዚህ ዓመት ጥሩ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የተቋማትን መመዘኛ መስፈርት በመጠቀም ተቋማትን መመዘናቸውንም ተናግረዋል።
በቀጣይም መሰል ሥራዎችን በማጠናከር ከተቋማት ጋር በጋራ በመኾን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!