
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጻም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ መድረክ አካሂዶል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ኀላፊ የሺዋስ አንዱዓለም በ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ የተሠራበት እንደነበር ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን የጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ በተሠራው ሥራ ከ450 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የእናቶችና ሕፃናትን ጤና ለማሻሻል ባለፉት ጊዜያት በጸጥታ ችግር ምክንያት ተደራሽ ያልነበሩ ቦታዎች አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት። በበጀት ዓመቱ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ሰፊ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል።
በዞኑ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ምቹ እና ፅዱ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የሕዝብ መድኃኒት ቤቶችን በመገንባት ላይ መኾናቸውን አንስተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎችም በበጀት ዓመቱ የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በቀጣይም ቀልጣፋ የጤና አገልግሎቱን ለመስጠት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በ2018 በጀት ዓመት በወረዳዎች እና በአንዳንድ ተቋማት ላይ የታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ለማኅበረሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ በውይይት መድረኩ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!