ትብብር እና ቅንጅት የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

6

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር እና የቅንጅት መድረክ ተካሂዷል።

የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትብብር እና ቅንጅት ለሰላም ግንባታ፣ ለዘላቂ ልማት እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ ነው ተብሏል።

የአማራ ክልል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ንጋቱ ደስታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መቋቋም፣ የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትብብር እና ቅንጅት መኖር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ነው ያሉት።

ከመንግሥት ጋር ያሉ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ፣ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስጠበቅ ሥራዎችን በተገቢው መንገድ ለመሥራት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር እና የቅንጅት መድረክ ተግባብቶ ለመሥራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ተባብረው እና ተቀናጅተው ሢሠሩ የተቋቋሙበት ዓላማ የበለጠ ጎልቶ እንዲወጣ ያስችላል ነው ያሉት።

ጠንካራ የኾነ ትብብር እና ቅንጅት ሲኖር የማኅበረሰቡን ችግሮች ለማየት እና መፍትሔ ለማመላከት ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ቁርጠኞች መኾናቸውን አስታውቀዋል።

የሰላም ግንባታ እና የሽግግር ፍትሕ ውጤታማ እንዲኾን የበኩላቸውን እንደሚወጡም አንስተዋል።

የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ መሠረት እንዲይዝ ችግሮችን በጋራ ለመታገል እና የጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር መሰሶ ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለልማት፣ ለዲሞክራሲ ባሕል፣ ለሰላም ግንባታ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚሠሩ ናቸው ነው ያሉት።

ባለፉት ጊዜያት በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ ሕግ እና የፖሊሲ አሠራር ስለነበር የሲቪል ማኅበራትን ሚና ወደ ኋላ የጎተተ፣ ሀገርን እና ሕዝብን ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተጠቃሚ እንዳይኾኑ ያደረገ ነበር ብለዋል።

አሁን ላይ የወጣው አዋጅ ግን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር መሰሶ ናቸው ብሎ የሚመለከት እንደኾነም አብራርተዋል።

መንግሥት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አውንታዊ ዕይታ ሲኖረው ቅንጅት እና ትብብር አስፈላጊ መኾኑን ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በመንግሥት መካከል አዲስ አስተሳሰብ እንዳለም ገልጸዋል።

የቀደመው አዋጅ ሲቀር የእሳቤ ለውጥም ተደርጓል፣ ከአዲሱ እሳቤ ጋር የሚሄድ አሠራርም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ቅንጅት እና ትብብር የማኅበረሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እና እንደ ሀገር ያሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል። በተናጥል መሄድ አዋጭ አለመኾኑንም አንስተዋል።

የዲሞክራሲ ባሕል እንዲገነባ እና ከግጭት ይልቅ በውይይት የሚያምን ማኅበረሰብ ለመገንባት ቅንጅት እና ትብብር ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የማኅበረሰብ ልማትም ኾነ የማኅበረሰብ ችግር የጋራ ጉዳዮች መኾናቸውንም አንስተዋል።

ሰላምን በጋራ ለመጠበቅ፣ ሕዝብን የሚጠቅሙ አሠራሮችን ለማበጀት እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ግንባታ፣ በዘላቂ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች በቁርጠኝነት ለመሥራት ዝግጁ መኾናቸውንም አመላክተዋል።

የማኅበረሰብ ችግሮች ላይ እንደሚያገቧቸውም ተናግረዋል።

ማኅበረሰቡ በችግር ውስጥ ኾኖ ዝም ሊሉ እንደማይችሉ እና ከወትሮው በተለዬ በተነሳሽነት እና በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰላምን የመረጡ የታጣቂ መሪዎች እና አባላቱ ወደ አካባቢያቸው ተመለሱ።
Next articleበጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የተደራሽነት ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።