የተዳፈነው እሳት

9

ባሕር ዳር፦ ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኤች አይ ቪ ኤድስ የዓለም ሥጋት ኾኖ መቀጠሉን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በዓለም ላይ ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንዳለባቸው ድርጅቱ በ2024 መጨረሻ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል። በዚሁ ዓመት 630 ሺህ ሰዎች ከኤች አይቪ ጋር በተያያዘ ሕይዎታቸው አልፏል።

ከፍተኛውን ሥርጭት አፍሪካ የሚይዝ ሲኾን በተለይም ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጀሪያ፣ ሌሴቶ እና ቦትስዋና ደግሞ ከፍተኛ ተጠቂ ናቸው።

በኢትዮጵያም በሽታው አሁንም አሳሳቢ ነው። በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ውድነህ ገረመው በአማራ ክልል እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየው የበሽታው ስርጭት 1 ነጥብ 09 በመቶ እንደኾነ አንስተዋል።

ይህም ከሀገሪቱ አማካይ ሥርጭት በዜሮ ነጥብ 19 ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት። በክልሉ በወረርሽኝ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የሥርጭት ምጣኔው ተጋላጭ በኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ መጨመር አሳይቷል። በክልሉ 84 ወረዳዎች ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭ ኾነው ተለይተዋል። ክልሉ በተከሰተው መፈናቀል፣ ጾታዊ ጥቃት፣ የትምህርት ቤቶች መቋረጥ ለሥርጭቱ መጨመር እንደምክንያት ተቀምጧል።

በአማራ ክልል አሁን ላይ 173 ሺህ 442 የሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንዳለ ያነሱት ዳይሬክተሩ ከእነዚህ ውስጥ 92 በመቶ የሚኾኑት ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁ ናቸው። ከተመረመሩት ውስጥ ደግሞ 99 በመቶ የሚኾኑት ሕክምና መጀመራቸውን ነግረውናል።

አሁንም የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ፈጠራ እንደተጠበቀ ኾኖ ይበልጥ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የባሕርይ ለውጥ ሥርጸት እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል። ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው የተገኘባቸውንም በመለየት ሕክምና እንዲጀምሩ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት።

የኤች አይ ቪ ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሲደረጉ የነበሩ ድጋፎች መቀነስ ችግር ቢያጋጥምም በአካባቢ ሃብት በማሰባሰብ ተጋላጭ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከአጋላጭ ሥራዎች እንዲወጡ እየተሠራ ይገኛል።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የመመርመሪያ ኪቶችን እና መድሃኒቶችን ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ፈታኝ እንደነበርም ገልጸዋል።

“ኤች አይ ቪ አሁንም የተዳፈነ እሳት ነው” ያሉት ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት በክልሉ የተከሰተውን የሰላም ችግር በመቅረፍ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ኑሮ እንዲኖሩ ቢደረግ ቫይረሱን የመቀነስ እድል እንደሚኖር ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሚሠራው ሥራ ባለፈ የሃይማኖት ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና ሁሉም ማኅበረሰብ ኀላፊነትን በመውሰድ ድርሻን መወጣት ያስፈልጋል ተብሏል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት፣ በዘላቂ ልማት እና በሰላም ግንባታ ሂደት እየተሳተፉ ነው።
Next articleሰላምን የመረጡ የታጣቂ መሪዎች እና አባላቱ ወደ አካባቢያቸው ተመለሱ።