
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) አትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ እ.አ.አ እስከ 2024 ከማንኛውም ውድደር መታገዱን ብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤትን ጠቅሶ ባወጣው መረጃ መሠረት አትሌት ወንድወሰን ከተማ በታኅሳስ 2019 በቻይና ተካሂዶ በነበረው የግማሽ ማራቶን ውድደር በግሉ መሳተፉን አስታውሷል፡፡
በዚህ ውድደር ወቅት በሰጠው ናሙና አበረታች ንጥረ ነገር መጠቀሙ በምርመራ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አትሌቱ ለአራት ዓመታት ከማንኛውም የአትሌቲክስ ውድድር መታገዱ ይፋ ተደርጓል፡፡ ቅጣቱ ከ01/02/2020 ጀምሮ በቀን 01/02 2024 ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በኢትዮጵያ ንፁህ የአትሌቲክስ ስፖርት እንዲስፋፋ የሚያካሂደውን የግንዛቤ ማሳደግ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ ህገ ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ አትሌቶችን ከብሔራዊ ፀረ አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ጎን በመቆም እንደሚያወግዝም ነው ያስታወቀው፡፡
አትሌቶችም ከራሳቸው አቅምና ብቃት ውጭ ምንም ዓይነት አበረታች ቅመም እንዳይጠቀሙ፣ ተግባሩ ለሃገርም ሆነ ለአትሌቶች ስም መጉደፍ አሉታዊ ሚናው ከባድ በመሆኑ ራሳቸውን ከዚህ ድርጊት እንዲያርቁ ጥሪ አቅርቧል።