የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት፣ በዘላቂ ልማት እና በሰላም ግንባታ ሂደት እየተሳተፉ ነው።

10

ባሕር ዳር: ሐምሌ 18/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር እና የቅንጅት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አታላይ ጥላሁን በአማራ ክልል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መመሥረቱን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ እውን እንዲኾን በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን የተናገሩት ምክትል ኀላፊው የሲቪል ማኅበረሰብ ምክር ቤቱ መመሥረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ያስችለዋል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ከ181 በላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዳሉም ተናግረዋል። የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶቹ ከ337 በላይ ፕሮጄክቶችን እንደያዙ የተናገሩት ምክትል ኀላፊው ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ይዘው እንደሚንቀሳቀሱም አንስተዋል።

በአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት፣ በዘላቂ ልማት እና በሰላም ግንባታ ሂደት ተሳትፎ እንዳላቸው ነው የተናገሩት።

ድርጅቶቹ በአንድ በኩል በውስጣቸው በትብብር እና በቅንጅት እንዲሠሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንግሥት ጋር መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር እና የቅንጅት መድረክ በዘላቂነት ሊሠራበት እንደሚገባም ነው ያነሱት።

የትብብር እና የቅንጅት መደረኩ ውጤታማ እንዲኾን ሁሉም ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር የዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ አማካሪ መስፍን አበጀ ( ዶ.ር) የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የትብብር እና የቅንጅት መድረክ ከፌዴራል ጀምሮ በተደራጀ መልኩ እየተመራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በለውጡ ዓመታት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ለማጠናከር ውጤታማ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው የገለጹት።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በሰላም ግንባታ፣ በግጭት አፈታት፣ በዜጎች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት፣ በዲሞክራሲ ባሕል ግንባታ ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ ሚናቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ የሪፎርም ሥራዎች መሠራታቸውን እና ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምቹ ኹኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል። የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚያስችል አውድ መፈጠሩንም አንስተዋል።

ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎች ክልላዊ አጀንዳዎች ላይ ተሳትፏቸው እንዲጨምር የሚያስችል አውድ እየተፈጠረ መጥቷልም ነው ያሉት።

ሲጫወቱ የቆዩትን አውንታዊ ሚና በተሻለ መንገድ ከፍ ለማድረግ እንዲያስችል የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ የቅንጅት እና የትብብር መድረክ ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል።

የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ትብብር እና ቅንጅት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ፣ ለኅብረተሰብ ተጠቃሚነት፣ ለዴሞክራሲ ባሕል ምሕዳር መስፋፋት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የትብብር እና የቅንጅት መድረኩ ራሱን በቻለ አደረጃጀት እንደሚመራም ተናግረዋል። እስከታችኛው መዋቅር ድረስ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የመንግሥት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ትብብር እና ቅንጅት በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላም መስፈን፣ ለልማት እና ለኅብረተሰብ ተጠቃሚነት ሚናን መወጣት ይገባል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሃይማኖት አባቶች ለሰላም በመቆም አባታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
Next articleየተዳፈነው እሳት