
ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ”ሰላማችንን እንጠብቃለን፣ ልማታችንን እናረጋግጣለን” በሚል መሪ መልዕክት በከተማዋ ከሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ከተማ አሥተዳደሩ ከግጭት አዙሪት ወጦ ልማትን በማስፋት የነዋሪዎቹን ሕይወት ለማሻሻል እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶች ከፈጣሪ በተሰጣቸው ሥልጣን ለሰላም በመቆም አባታዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ የጠየቁት ከንቲባው ሁላችንም የቆምንለት አላማ ሰላም እና ልማት በመኾኑ ለዘላቂ ሰላም በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች እየታየ ያለው ግጭት እንዲቆም እና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በየሃይማኖታቸው የድርሻቸውን እያበረከቱ መኾኑን ተናግረዋል። ለሰላም ፅኑ አቋም አለን ያሉት የሃይማኖት አባቶቹ ሰላሟ የተጠበቀች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ ችግሮችን በመመካከር እና በውይይት እንዲፈቱ መሥራት አለብን ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ አማካሪ በድሉ ድንገቱ መንግሥት የጸጥታ ችግሩን በውይይት ለመፍታት እየሔደበት ያለው ተግባር የበለጠ ውጤታማ እንዲኾን እና በሁሉም አካባቢ ልማት እንዲረጋገጥ አባቶች የተጣለባቸውን አባታዊ አደራ እንዲወጡ ጠይቀዋል። በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ያሉ አካላትን በመገሰፅ እና በማስተማር ትውልድን ለማዳን እንዲሠሩም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!