
አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የ2017 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጻም እና የ2018 ዓ.ም የሀገራዊ የልማት ዕቅድን በተመለከተ ተጠሪ ተቋማት ከኾኑት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት እና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ጥሩማር አባተ በ2017 በጀት ዓመት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት መረጃዎች በተሻለ ጥራት እንዲሰነዱ እና የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲተገበር ያደረገበት ነው ብለዋል።
እነዚህ ተግባራትም ለ2018 በጀት ዓመት መልካም ተሞክሮዎች የተወሰዱበት እንደኾነም አንስተዋል።
በተለይ በኢኮኖሚው ዘርፍ ዓለማቀፍ አዝማሚያዎችን ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ እና ስትራቴጅን ለመንደፍ የባለፈው ዓመት ተግባራት እንደመነሻ ይኾናሉ ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም በኢኮኖሚው ዘርፍ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና መሰል ጸጋዎች ላይ በሰፊው ለመሥራት መታቀዱንም አንስተዋል።
እንደ ሀገር በ2018 በጀት ዓመት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚመረቅበት፣ ሀገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት እና በርካታ ሁነቶች የሚከወኑበት እንደመኾኑ መጠን የእነዚህን ሁነቶች የተተነተነ መረጃን በቴክኖሎጅ አግዞ መያዝ፣ ለሀገራዊ የልማት ፖሊሲ መነሻ እንዲኾኑ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ አዲሱ ዳዊት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን