የእርሻ መሬታቸው እንዲመለስላቸው በቅርቡ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች ጠየቁ፡፡

244

የክልሉ መንግሥትና ኮማንድ ፖስት ደግሞ የእርሻ መሬቶችን እያስመለሱ፣ የመጠለያ ችግሮችም እንዲቀረፉ እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 27/2012 ዓ.ም (አብመድ) ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ተጠልለው ከነበሩት ከ49 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ወደ ቀደመው ኑሯቸው እስከሚመለሱ ድረስም የዕለት ቀለብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ሁኔታዎች እንደሚመቻቹላቸው ከአማራ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥታት ተገልጧል፡፡ የፀጥታ ስጋት እንዳይፈጠር ለማድረግም ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ መዋቅሮች የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው መግባባት እንደተፈጠረ እየተገለጸ ነው፡፡

ወደ ቀያቸው ከተመለሱት መካከል ከመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ለአብመድ አስተያየት የሰጡት ነዋሪዎች የሰላሙ ሁኔታ ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የእርሻ መሬት ይዞታቸውን መነጠቃቸውን፣ ማሳውንም ‘ቀጣይ ዓመት እንለቃለን፤ ዘንድሮ ግን አንለቅም’ የሚሉ መኖራቸውንና ይህም እንዲስተካከልላቸው ጠይቀዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ መሬታቸው እንዲመለስላቸው አቅጣጫ ቢያስቀምጥም እስካሁን ያልተመለሰላቸው ብዙዎች እንደሆኑም ነው አስተያየየት የሰጡት፡፡

በቻግኒ ተጠልለው ከነበሩትና በቅርቡ ወደ ማንዱራ ከተመለሱት መካከል አስተያዬት የሰጡት ደግሞ አቀባበሉ መልካም የሚባል ቢሆንም አብዛኞቻቸው መጠለያ እንደሌላቸው ነው የተናገሩት፡፡ ለጊዜያዊ መጠለያነት የተሰጣቸው ሸራም ክረምቱን ለማሳለፍ እንደሚያስቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የፀጥታው ሁኔታ ያለስጋት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት በሚችሉበት ደረጃ እንዲሆንላቸው፣ መጠለያም እንዲገነባላቸው ጠይቀዋል፡፡

የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ኮሎኔል ረሽድ ኢብራሂም “እስካሁን በተሠራው ሥራ ኅብረተሰቡን ወደ ነበረበት ቀዬ ከመመለስ ጀምሮ አጥፊዎችን በማኅረሰቡ ጠቋሚነት በቁጥጥር ስር አውለናል፡፡ የነበረው ግጭትም ቆሟል፤ ይህን ያደረገው ደግሞ ማኅበረሰቡ ከእኛ ጋር በጋራ በሠራው ሥራ ነው” ብለዋል፡፡ የፀጥታ ስጋት ሙሉ ለሙሉ እንደተቀረፈ፣ የእርሻ ማሳቸው እየታረሰና ቤትም እየተሠራላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሌሎች የታረሰውን እርሻ እስከነ ሰብሉ የመመለስ ሥራም የሚሠሩ ሰዎች እንዳሉም ሌተናል ኮሎኔል ረሽድ ተናግረዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ማኅበረሰቡን የማስማማት፣ በግለሰብ ደረጃ ያሉ ቅራኔዎችን የመፍታት ሥራ እየሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ቀሪ ሥራዎችን ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን እንደሚያከናውኑ ነው የተናገሩት፡፡

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው የፈረሱ ቤቶችን የመገንባት ሥራው በሕዝብ ተሳትፎ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእርሻ መሬታቸውም እየተመለሰ መሆኑን፣ ይህም ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ፎቶ፡- ከድረገጽ

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleየአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጀመረ፡፡
Next articleአትሌት ወንድወሰን ከተማ ማሞ ለአራት ዓመታት ከውድደር ታገደ፡፡