በበጀት ዓመቱ 262 መሥሪያ ቤቶች ኦዲት ተደርገዋል።

15

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2017 በበጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ለአማራ ክልል ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

ሪፖርቱን ያቀረቡት የአማራ ልልል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አማረ ብርሃኑ (ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ የተለያዩ እቅዶችን በማቀድ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል። የተቋሙን ሠራተኞች በ15 ቡድኖች በማደራጀት የለውጥ እና የአበይት ተግባራትን ማከናዎን መቻሉን አንስተዋል።

መሥሪያ ቤቱን ነፃ እና ገለልተኛ ኾኖ እንዲሠራ የሚያስችሉ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ማዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ለ253 ኦዲተሮች ሥልጠና በመስጠት የባለሙያዎችን አቅም የማሣደግ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። የሥጋት ተጋላጭነት አሥተዳደር ሥርዓት ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

በተቋሙ 56 የኦዲት ቡድኖችን አደራጅቶ በማሠማራት 262 መሥሪያ ቤቶችን ኦዲት ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር በአፈጻጸሙ ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረም አመላክተዋል።

ለክልሉ ከተመደበው በጀት 44 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የሚኾነውን በኦዲት አገልግሎት ሽፋን መስጠት እንደተቻለ ገልጸዋል። የኦዲት ሽፋኑ በማዕከል፣ በዞን፣ በወረዳ እና በከተማ አሥተዳደር ደረጃ የተለየ መኾኑን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ ተቋማት የኦዲት ግኝት ምላሽ እንዲሰጡ ከተጠየቁት 230 መሥሪያ ቤቶች መካከል 123 ተቋማት ምላሽ መስጠታቸውንም አመላክተዋል።

24 ተቋማት ዘግይተው ምላሽ የሰጡ መኾናቸውን ነው የገለጹት። 67 ተቋማት ደግሞ ምንም ምላሽ አለመስጠታቸውን በሪፖርታቸው አብራርተዋል።

ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በሠራው ሥራ በሀገሪቱ ካሉት ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች ጋር ተወዳድሮ የተሻለ አፈጻጸም ማግኘቱንም አንስተዋል። በተገኘው ውጤት ምክንያትም ዓለም አቀፍ የኦዲት ማሠልጠኛ ተቋም በአማራ ክልል እንዲኖር ፈቃድ ተሰጥቷል ነው ያሉት።

የበጀትና የሰው ኀይል እጥረት፣ የኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ትብብር ማነስ፣ የተቋማት የሥራ ኀላፊዎች በኦዲት መግቢያ እና መውጫ ስብሰባዎች አለመገኘት በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች መኾናቸውን አስረድተዋል።

የመሥሪያ ቤቱን አዋጅ ማሻሻል፣ የኦዲት ሽፋንን ማሳደግ፣ የኦዲት ሪፖርት ምላሽ አሰጣጥ እና እርምጃ አወሳሰድ ላይ መሥራት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኾናቸውን አብራርተዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተቋማት የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ተግባራዊ በማድረግ ለተሻላ አሠራር ሊተጉ እንደሚገባ የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡
Next articleመረጃዎችን በአግባቡ በመሰነድ ለሀገራዊ የልማት ዕቅድ እና ፖሊሲ አቅጣጫዎች መሠረት መጣል ተገቢ ነው።