ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ ክንውን ገምግሟል፡፡ የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ሃናን አብዱ የተገመገሙ ተቋማት ባላቸው አፈጻጸም የታዩ ጥንካሬዎችን እና መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል፡፡
ከተገመገሙ ተቋማት መካከልም ገቢዎች ቢሮ አንዱ ነው፡፡ ገቢዎች ቢሮ በችግር ውስጥ ኾኖም የሠበሠበው ገቢ የሚበረታታ መኾኑ በጥንካሬ ተቀምጧል፡፡ ገቢን በአግባቡ ለመሠብሠብ የኢ-ታስ ግብር ከፋዮች ባሉበት ቦታ ኾነው የግብር ክፍያቸውን መፈጸም የሚያስችል አሠራር መዘርጋቱንም አንስተዋል፡፡ የንግድ ግብር ከፋዮችን ቁጥር ወደ 401ሺህ 396 ማሳደግ መቻሉ በጥንካሬ የሚገለጽ እንደኾነም ነው የገለጹት፡፡
ሕገ ወጥነትን በሚገባ አለመከላከል፣ ቅንጅታዊ ሥራው የላላ መኾኑን እና መረጃዎችን በአግባቡ አለመሠብሠብ መሻሻል የሚገባቸው ተብለው ከተነሱት መካከል ናቸው፡፡
ሌላው የተገመገመው ተቋም ገንዘብ ቢሮ ነው። የወረዳዎችን፣ የዞኖችን እና የከተማ አሥተዳደሮችን የተሽከርካሪ ችግሮች ለመፍታት ከ400 በላይ ተሽከርካሪዎች ድጋፍ ማድረጉ በጥንካሬ ተነስቷል፡፡
የወረዳዎችን የበጀት ዕጥረት ለመፍታት እንዲቻል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እና ድጋፍ መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡ የክልሉን የልማት ክፍተት ሊሞሉ ከሚችሉ ፕሮጅክቶች ጋር ስምምነት መደረሱ እና 15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያላቸውን ፕሮጀክቶች ወደ ክልሉ በማምጣት የልማት ሥራዎች እያከናወኑ መኾኑ የተሻለ አፈጻጸም እንደኾነም ነው የተብራራው፡
በርካታ ተሸከርካሪዎች እና ብረታ ብረት በዞኖች፣ ወረዳዎች እና በክልሎች ተቋማት በየቦታው ወድቀው ከአገልግሎት ውጭ በመኾናቸው እና ለዚህም መፍትሔ አለመሰጠቱ እንዲታረም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ቢሮዎች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በጀታቸውን አዘጋጅተው ሳያቀርቡ ሲቀሩ የማስተካከያ ርምጃ አለመወሰዱ መስተካከል እንዳለበትም አመላክተዋል።
የፕላን እና ልማት ቢሮ የክልሉን የ25 ዓመታት የአሻጋሪ ዕድገት እና የዘላቂ የልማት ዕቅድ ለማስተግበር የሚያስችል የክልሉን የጅኦ ስፓሻል ዕቅድ እና የካፒታል ፕሮጀክት ሃብት ለክልሉ ልማት እንዲውል የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱ በጥንካሬ ተነስቷል፡፡
የክልሉን አጠቃላይ የልማት አመልካች ዓመታዊ መረጃዎችን በማሠባሠብ መተንተ፣ የክልሉ የሰብዓዊ ልማት አመልካች የኾኑ የትምህርት እና ጤና መረጃዎችን በመሠብሠብ ትንተና መሠራቱ በጥንካሬ የሚነሳ ነው ተብሏል።
የካፒታል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እና በጀት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራው ዝቅተኛ በመኾኑ ሊሻሻል እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
የከተሞችን ዕድገት ጥናት በማጠናቀቅ የከተማ ልማትን ሳይንሳዊ በኾነ እና የረዥም ዓመት ራዕይ ይዘው እንዲሠሩ ለማድረግ ትኩረት አለመሰጠቱ ሊስተካከል ይገባል ነው ያሉት፡፡
የተገመገሙ ተቋማት የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ተግባራዊ በማድረግ ለተሻላ አሠራር ሊተጉ እንደሚገባም ሠብሣቢዋ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!