በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 370 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ጥቅል ምርት ተገኝቷል።

11

ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ፣ ገንዘብ ቢሮ እና የፕላን እና ልማት ቢሮ ለበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሥራ አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል።

የአቋሚ ኮሚቴው አባላት የሀሰተኛ ደረሰኞች ግብር ከፋዩን እየጎዳው በመኾኑ መፍትሔ መቀመጥ እንዳለበት አንስተዋል። በገቢ አሰባሰቡ ከአዲሱ ሲስተም ጋር በተያያዘ በግብር ከፋዩ ላይ መጉላላት እንዳይኖር መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተጣለው የደረጃ “ሐ” ቁርጥ ግብር ጥናት አቅምን ያላገናዘበ መኾኑን ችግሮችን በማስከተሉ ቅሬታዎች እየተነሱ ነው ብለዋል።

ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ ክብረት ማህሙድ የሃሰተኛ ደረሰኝ ችግር ሀገራዊ በመኾኑ በፌደራል እና በክልሎች ቅንጅት የሚፈታ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በየክልሉ ይታተም የነበረው ደረሰኝ እንደ ሀገር በአንድ መለያ ኮድ ለማሳተም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡

በአዲሱ ሲስተም ጋር በተያያዘ ችግር እንዳይፈጠር
የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። ሥልጠናዎችንም ሠጥተው ወደ ሥራ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡

በደረጃ ‘ሐ’ ግብር ከፋዮች ጋር የሚነሳውን ቅሬታ
ደረጃ በደረጃ እየታዩ እየተፈቱ መኾኑን ገልጸዋል። በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ተግባር መኾኑን አንስተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የኦዲት ግኝት አመላለስ ላይ ያሉ ችግሮች እንዲስተካከሉ አመላክተዋል። በእርዳታ እና ብድር የሚመጡ በጀቶችን መቆጣጠር እንደሚገባም ተነስቷል።

ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን መሐሪ (ዶ.ር) የኦዲት ግኝት አመላለስ ላይ ያሉ ችግሮች ለመፍታት በምክር ቤቱ የወጭ ቁጥጥር እና ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ተሰይሞ ለማስተካከል እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ሥራው የሁሉም ባለድርሻ አካላት መኾኑንም ተናግረዋል።

በእርዳታ እና ብድር የሚመጡ በጀቶችን በተቀመጠለት አሠራር ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ለሌላ ዓላማ ውለው የተገኙትን ደግሞ ማስረጃን መሰረት በማድረግ የማስመለስ ሥራ መሠራቱንም ነው ያነሱት፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በፕላንና ልማት ቢሮ በኩል እንደ ክልል ማክሮ ኢኮኖሚው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠይቀዋል።

የፕላን እና ልማት ቢሮ አማካሪ ሙሉቀን አዳነ (ዶ.ር)
በ2017 በጀት ዓመት ጥቅል ክልላዊ ምርት 370 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ምርት መገኘቱን ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበቱም እስከ ጥር 2017 ዓ.ም ድረስ 14 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት እየሠራ ነው።
Next articleተቋማት የተሰጣቸውን ግብረ መልስ ተግባራዊ በማድረግ ለተሻላ አሠራር ሊተጉ እንደሚገባ የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡