
ባሕር ዳር: ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ አማካሪ ሙሉቀን አዳነ (ዶ.ር) ለበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
የፕላንና ልማት ቢሮ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅዶችን አቅዶ አፈጻጸማቸውን የመከታተል ሥራ በሰፊው ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት የክልሉን ስትራቴጂካዊ መረጃ ለማደራጀት እና የአጠቃቀም ሥርዓትን ለመዘርጋት በርካታ ሥራዎች እንደተሠሩ በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡
የክልሉን የመረጃ ዝግጅት እና አጠቃቀም ሥርዓት ማሻሻል ላይ የታቀዱ ተግባራትን ሙሉ በሙሉ ማከናወኑንም ገልጸዋል፡፡
ከነዚህም መካከል የአምስት ዓመት የጅኦ ስፓሻል መረጃ፣ የሴክተሮች መረጃ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የክልሉን ነባራዊ ኹኔታ ያገናዘበ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እና የ25 ዓመቱን ፍኖተ ካርታ እንዲታቀድ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አንስተዋል፡፡
በዕቅዶች የሥነ ሕዝብ ጉዳዮችን ተካተው እንዲታቀዱ አፈጻጸሙን ለመከታተል እና ለመደገፍ የተያዘው ዕቅድ መከናወኑም ተነስቷል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት የክልሉን ሕዝብ ብዛት በዕድሜ ክፍፍል በመተንበይ መረጃውን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የሥነ ሕዝብ ጉዳይ በሴክተሮች የልማት ዕቅድ እንዲካተት የማድረግ ሥራ መሠራቱም በሪፖርት ተመላክቷል፡፡
የ2016 በጀት ዓመት የክልሉ ኢኮኖሚ ወይም ጥቅል ምርት ዓመታዊ ሥራ በዕቅዱ መሠረት መተግበሩንም ገልጸዋል፡፡ የክልሉን ማክሮ ኢኮኖሚ አመላካች ጽንሰ ሀሳብ ሰነድ በማዘጋጀት ተደራሽ ለማድረግ እንደተቻለ ነው የተገለጸው፡፡
የክልሉን የአምስት ዓመት ዕቅድ እና የ25 ዓመቱን ፍኖተ ካርታ ለመተግበር የክልሉን መዋቅር በአዲስ ተጠንቶ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
የክልሉን የአምስት ዓመታት ዕቅድ ማስፈጸሚያ 16 ስትራቴጂክ ዶክመንቶች ተዘጋጅተዋል ነው ያሉት፡፡ ጥናትና ምርምርን ለማጎልበት የክልሉን መዋቅር ከቀበሌ እስከ ክልል በአዲስ የማስጠናት ሥራ መከናወኑም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የክልሉን ማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ያለውን የትንተና ሥራ የ29 ዓመታት ተከታታይ መረጃ በመሰብሰብ ለድህነት ቅነሳ ዓላማ አድርጎ ለመሥራት በሚያግዝ መልኩ እንደተሠራ ተጠቅሷል፡፡
የክልሉ የዕቅድ አፈጻጸም የድጋፍና ክትትል ሥርዓት በተመለከተ የዞኖች ዕቅድ፣ የመልካም አሥተዳደር፣ የካፒታል ፕሮጀክት ዕቅድ፣ የረጅም ጊዜ፣ የአጭር ጊዜ እና የበጀት ዕቅድ በአግባቡ እንዲታቀድ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በየደረጃው ላሉ አካላት የአምስት ዓመት መሪ ዕቅዱን የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱ የተገለጸ ሲኾን ለ270 የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ጨምሮ እስከ ታች ድረስ የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በክልሉ የሚተገበሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመለየት መረጃዎችን የማጠናከር ሥራ በዕቅዱ መሠረት መከናወኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!