የፓለቲካ ልሂቃን ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት የሰላም ሚናቸውን እንዲወጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።

15

አዲስ አበባ፡ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላምን በማጽናት የፓለቲካ ፓርቲዎች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በጋራ ባዘጋጁት መድረክ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የተለያዩ የፓለቲካ ልሂቃን እና የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሰላም ልማትን፣ ነፃነትን እና ፍትሕን ያለምንም እንቅፋት የማግኘት መብት መኾኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይረጋገጥ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ ጉዳዮች ችግር ሁነው መቆየታቸውን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ችግሮች እልባት መስጠት ለሰላም ግንባታ ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል።

አብዛኞቹ ሰው ሠራሽ ችግሮች ከዲሞክራሲ ባሕል አለመዳበር የሚመጡ በመኾናቸው የፓለቲካ ልሂቃን ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት የሰላም ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ ተቋሙ ሰላምን ለማጽናት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

አሁን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማጽናትም የፓለቲካ ፓርቲዎች ኀላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሣቢ ሰለሞን አየለ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ከእርስ በእርስ የጦርነት አዙሪት ተላቃ ግጭቶች እንዲቆሙ ለማስቻል ውይይቶች መደረግ አለባቸው ብለዋል።

ምክር ቤቱ የዳበረ እና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።

በመድረኩ በሰላም እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ ያተኮሩ ለውይይት መነሻ የሚኾኑ ጹሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየብስክሌት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እየተሠራ ነው።
Next articleየአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ለመዘርጋት እየሠራ ነው።