የብስክሌት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እየተሠራ ነው።

10

ባሕርዳር፡ ሐምሌ 16/2017ዓ.ም (አሚኮ) የባሕርዳር ከተማ ነዋሪው ካሰኝ ንጋቱ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች የሚኾን መንገድ በኮሪደር ልማቱ ተለይቶ መሠራቱ ለከተማዋ ሕዝብ የቆየ ብስክሌት የመጠቀም ባሕል ዋጋ የሰጠ ተግባር እንደኾነ ነገሩን፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ እንደኾኑና ወደ ቢሮ ሲገቡ እና ሲወጡ ብስክሌት እንደሚጠቀሙ የገለጹት አቶ ካሠኝ እንደ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንደሚጠቀሙበት እና ከጤና አንጻርም ይጠቅመኛል ብለዋል።

ሰዎች ብስክሌትን ሲጠቀሙ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻርም ጠቀሜታ እንዳለዉ የተናገሩት ሃሳብ ሰጪው ባሕር ዳር ቀደም ሲል የምትታወቅበት የብስክሌት እንቅስቃሴ እንደነበርና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት በከተማዋ ሲጀመር አብዛኛዉ ሰዉ የባጃጅ እና ታክሲ ተጠቃሚ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡

አኹን የተሠራዉ የብስክሌት መንገድ ውብ እና በጣም ምቹ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ አብዛኛዉ ሰዉ በቀጣይ ብስክሌትን በስፋት ይጠቀማል ብለዉ ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪና የብስክሌት ስፖርተኛው አብርሃም የኋላእሸት ራሱን ችሎ የተሠራዉ የብስክሌት መንገድ ያለምንም የደህንነት ችግር ለማሽከርከር አመቺ ነው።

ስለኾነም ተተኪ የብስክሌት ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት የሚያነሳሳ እንደኾነ እና ለነባር ብስክሌት ስፖርተኞችም ጥሩ መነቃቃት እንደፈጠረ ነዉ የነገረን፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቶማስ ታምሩ በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የብስክሌት መንገድ ፕሮጀክቶች ስፖርቱን ታሳቢ አድርገዉ እየተገነቡ መኾናቸዉን አንስተዋል።

የብስክሌት እንቅስቃሴ አኹን ላይ መቀዛቀዙን አንስተው የተሠራው የኮሪደር ልማት የብስክሌት እንቅስቃሴን ለማነቃቃት አስተዋጽኦ እንዳለዉ ገልጸዋል፡፡

ብስክሌትን እየተጠቀመ ጤናዉን የሚጠብቅ ማኅበረሰብ ለመፍጠር እና ታዳጊዎችን በየእድሜ ክልላቸዉ በዘርፍ እያሠለጠኑ የብስክሌት ዉድድር ላይ እንዲሳተፉ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየተሠሩ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የተጠናከረ የብስክሌት እንቅስቃሴ በነበረበት ጊዜ ክለብ ተመስርቶ እና ሥልጠናዎች እየተሰጡ ዉድድር ሲካሄድበት በነበረዉ ልክ ሳምንታዊ የብስክሌት ዉድድሮች እንዲካሄዱ ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ እንደኾኑም ጠቁመዋል።

ይህም የከተማዋን የቀደመ የብስክሌት እንቅስቃሴ ለመመለስ የሚያስችል አንዱ መንገድ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋን የብስክሌት እንቅስቃሴ ወደ ቀደመ ኹኔታዉ ለመመለስ የከተማ አሥተዳደሩን እና የኗሪዎችን እገዛ ይጠይቃል ያሉት አቶ ቶማስ ቀጣይ የብስክሌት ተወዳደሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እንሠራለን ብለዋል፡፡

አኹን ላይ የብስክሌት ዋጋ እንደተወደደ የተናገሩት ኃላፊዉ ችግሩን ለመቀነስ ቀደም ሲል በርከት ያሉ ብስክሌቶች ተገዝተው ለተቋማት እንደተሰጡ ጠቁመዋል።

ይህንን ለማጠናከርም መንግሥታዊ ያልኾኑ እና የመንግሥት ተቋማትም አጋዥ መኾን እንዳለባቸዉ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየባሕር ዳር ከተማን መሠረታዊ ችግሮች ይፈታሉ የተባሉ ውሳኔዎች ተላለፉ።
Next articleየፓለቲካ ልሂቃን ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት የሰላም ሚናቸውን እንዲወጡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።