
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አሚኮ በቅርቡ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መሬት ላይ እየታዩ ያሉ ብልሹ አሠራሮችን መሠረት በማድረግ “የአጥር ኢንቨስትመንት” በሚል ርእስ የምርመራ ዘገባ መሥራቱ ይታወሳል።
ይህን የመልካም አሥተዳደር ችግር የዳሰሰውን ዘገባ የተመለከተው የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ ችግሮችን ለመፍታት ሲሠራ ቆይቶ ችግሮችን ይፈታሉ ብሎ ያመነባቸውን ውሳኔዎችን አሳልፏል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ኮሚቴ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው ሥብሠባም ለከተማዋ ነዋሪዎች የዘመናት የመልካም አሥተዳደር ችግር መንስኤ የኾኑ ሁለት አንኳር ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ነው የገለጸው። እነዚህ ውሳኔዎች የከተማዋን ዘላቂ ልማት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታሳቢ የተደረጉ መኾናቸውም ተመላክቷል።
የከንቲባ ኮሚቴው ትኩረት የሰጠው የመጀመሪያው ጉዳይ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በተለያዩ ጊዜያት በሕጋዊ መንገድ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል መሬት በግልጽ ጨረታ እና በምደባ ወስደው ያላለሙ ብሎም ከተሰጣቸው ዓላማ ውጭ ለሌላ ተግባር ያዋሉ ባለሃብቶች ጉዳይ እንደኾነም ተገልጿል።
እነዚህ ባለሃብቶች መሬቱን የወሰዱት ለራሳቸው እና ለቤተሰባቸው የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር፤ የከተማዋን የቱሪዝም እና የንግድ እንቅስቃሴ በማሳደግ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ታስቦ እንደነበርም ነው የጠቆመው።
ይሁን እንጂ ብዙዎች የመንግሥት እና የሕዝብ ሃብት የኾነውን መሬት ከወሰዱ በኋላ ለረዥም ጊዜ አጥሮ ማስቀመጥ፣ ግንባታ ጀምረው ሳያጠናቅቁ እና ከተሰጣቸው ዘርፍ ውጭ በሌላ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን ፈትሾ ማረጋገጡን ነው ያብራራው።
የከተማ አሥተዳደሩ ባለሃብቶቹ ወደ ሥራ እንዲገቡ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ምክክር በማድረግ፣ ተግሳጽ በመስጠት እና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ጥረት ቢያደርግም የሚፈለገው ውጤት መምጣት አልቻለም ብሏል።
በዚህም ምክንያት የከንቲባ ኮሚቴው ዝርዝር ውይይት ካደረገ በኋላ ከ205 ባለሃብቶች መካከል 143 ባለሃብቶች ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ጠቁሟል። እነዚህ ባለሃብቶች በተወሰነላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሥራ ካልገቡ መሬታቸው ሊነጠቅ እንደሚችልም አስገንዝቧል።
61 የመሬት ይዞታዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነጠቁ መወሰኑን የገለጸው ከተማ አሥተዳደሩ ከእነዚህ መካከል 30 ባዶ ቦታዎች እና 31 ደግሞ ጅምር ግንባታ የነበራቸው እንደኾኑም አስገንዝበዋል።
እነዚህ የተነጠቁ የመሬት ይዞታዎች ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱ የተወሰነ ሲኾን ለሌሎች አምራች ኢንቨስትመንቶች እንዲውሉ እንደሚደረጉም ነው ከተማ አሥተዳደሩ የጠቆመው።
ይህ ርምጃ የከተማዋን የመሬት ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም፣ ልማትን ለማፋጠን እና ግልጽነትን ለማስፈን ታሳቢ ተደርጎ የተወሰደ እንደኾነም ነው የተገለጸው።
በሌላ በኩል በ2000 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግሥት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎችን ለማበረታታት በማሰብ በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ማራኪ ቀበሌ የሰጠው 300 ካሬ ሜትር ቦታ ከመጀመሪያው ዓላማ ውጭ እና የመሬት መቀራመት የመሰለ አካሄድ መስተዋሉን ከተማ አሥተዳደሩ አንስቷል።
ከተማ አሥተዳደሩ ባደረገው ፍተሻም በአካባቢው 38 ብሎኮች እና 504 የተሸነሸኑ ቦታዎች ተገኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 341 ፋይል ያላቸው ሲኾኑ 151 ቦታዎች ደግሞ ክፍት ናቸው ብሏል። እነዚህ ክፍት ቦታዎች በሊዝ ጨረታ ወጥተው ለትክክለኛ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ መወሰኑንም ነው የጠቆመው።
12 ቦታዎች ላይ ግንባታ ቢኖርም ፋይል የሌላቸው በመኾናቸው ታጥረው ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱ ተወስኗል ነው ያሉት። በሕገ ወጥ መንገድ የተጀመሩ ግንባታዎችም እንዲወረሱ በሙሉ ድምጽ መወሰኑም ተገልጿል። ይህ ውሳኔ ከሕግ ውጭ የሚደረጉ ድርጊቶችን ለመግታት ያለመ እንደኾነም ነው የተብራራው።
እነዚህ የከንቲባ ኮሚቴው ውሳኔዎች የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር የመልካም አሥተዳደርን ለማስፈን፣ የመሬት ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀም፣ የከተማዋን ልማት ለማፋጠን እና የሕዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደኾነም ተጠቁሟል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን