የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጀመረ፡፡

762

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) አምስት ቢሊዮን ችግኞች የሚተከሉበት የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በመላው ኢትዮጵያ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የመርሀ ግብሩን መጀመር አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባስላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም እየሠራች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ዛሬ የሚከበረውን የዓለም የአካባቢ ቀን ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በማስጀመር እንደምታከብረውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

‘‘እንደሌላው ዓለም ሁሉ ኢትዮጵያም በአየር ንብረት ለውጥና በአካባቢ መራቆት እየተጎዳች ነው፤ እነዚህ ደግሞ ለአፈር መከላት፣ ጎርፍ፣ ድርቅና ሥነ ምኅደር መዛባት ያጋልጣል፤ ስለሆነም ይህንን ለውጥ መመከት የኛ ሥራ ሆኗል፤ ለዚህም ነው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን የምንጀምረው፡፡ ይህም በአራት ዓመታት የምንተክለው የ20 ቢሊዮን ችግኝ አካል ነው’’ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በመልእክታቸው፡፡

ባለፈው ዓመት ከተተከሉት የአረንጓዴ አሻራ ችግኞች 84 ከመቶ መጽደቃቸውን ያስታወሱት ዶክተር ዐብይ በዘንድሮው መርሀ ግብርም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ቅንጅት ግቡን ለማሳካት በሚያስችል ጥምረት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‘‘ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ የዓለም አካባቢ ቀንን ሲያከብር የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በመደገፍ እንዲሆን ጥሪየን አቀርባለሁ፤ ራሳችንን ከኮሮና ወረርሽኝ እየጠበቅን አረንጓዴ አሻራችንን እናኑር’’ ብለዋል ዶክተር ዐብይ በመልእክታቸው፡፡

ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቶች በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚኖሩም ታውቋል፡፡

በአብርሃም በዕውቀት

Previous articleአዲሱ የመሬት ካሳ ክፍያ መመሪያ ጸድቆ ወደ ተግባር አለመግባት በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ተቋማት ገለፁ፡፡
Next articleየእርሻ መሬታቸው እንዲመለስላቸው በቅርቡ ከአማራ ክልል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተመለሱ ተፈናቃዮች ጠየቁ፡፡