
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።
ቋሚ ኮሚቴው በሁለተኛ ቀን ውይይቱ በቀረበለት ሪፖርት ላይ ተነስቶ ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ያላቸውን ሀሳቦች በማንሳት የማጠቃለያ አስተያየት ሰጥቷል።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ እንዲኹም የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡትን ሪፖርት ተመስርቶ በተሰጠው ሀሳም ካለው የሥራ ፈላጊ ቁጥር ብዛት አኳያ የቀረበው የሥራ ዕድል ፈጠራ በቂ ነው ማለት አይቻልም ብሏል።
ለወጣቶች የሚሰጠው የሥራ ፈጠራ ሥራው ያመጣው ለውጥ ሊታይ እንደሚገባ የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ሼዶች ጉዳይም መታየት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
ኢንተርፕራይዞች የመሬት አቅርቦት ስለማያገኙ በሽግግር ሂደቱ ተስፋ እየቆረጡ እንደኾነም ነው የተገለጸው።
ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጸጋ ልየታ ላይ ምን ያህል በጥልቀት እየተሠራ እንደኾነ ሊፈተሽ ይገባዋልም ተብሏል።
ከማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አኳያ የንግድ ፈቃድ የጊዜ ገደባቸው ያጠናቀቁ እና በፈቃዳቸው መሠረት የማይሠሩትን ፈቃድ በመንጠቅ በኩልም መሠራት አለበት ነው የተባለው።
የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) አስተያየቶች ለቀጣይ ሥራ ጠቃሚ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ለወጣቶች የመጣን ተዘዋዋሪ ብድር በአግባቡ ለማበደር የባንክ ውስንነት መኖሩ የበለጠ ለመሥራት እንቅፋት መኾኑን ጠቁመዋል።
በሕገ ወጥ የተያዙ ኮንቴይነር እና ሼድ ማስመለስ መቻሉን፣ ለተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች አስፈላጊውን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን፣ የማይሠሩትን ፈቃድ ለመንጠቅ የቆየው ብልሹ ልማድ ማነቆ ቢኾንም በቀጣይ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አበባ ጌታሁን እሴት ሳይጨመርበት ከክልሉ የሚወጣ ማዕድን ጎጂ በመኾኑ በትኩረት እንደሚሠራ፣ የጊዜ ገደባቸው ያለቀ የማዕድን ባለፈቃዶች በቦታቸው ላይ እያመረቱ ከኾነ እንደሚታደስላቸው እና ባሕላዊው ግን የጊዜ ገደቡ ካለፈ እንደሚሠረዝ ነው ያብራሩት።
ኀላፊው ወጣቶች ሊሠማሩበት የሚገባውን ሥራ ላይ አላግባብ ባለሃብቶች እየተጠቀሙበት በመኾኑ በቀጣይም በክትትል እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ በላይ ዘለቀ በሁለቱም ተቋማት የሥራ ከባቢ ምቾት ፈጠራ እና የዲጂታላይዜሽንን ሥራዎችን አድንቀዋል።
የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ የብድር አቅርቦት እና ስርጭት፣ የሙያ እና ቴክኒክ ኮሌጆች ድጋፍ እና ክትትል እንዲኹም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጅምሮች በጥንካሬ ተነስተዋል።
ለወጣቶች የተዘዋዋሪ ብድር ገንዘብን ከያዘው ባንክ ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን መፍታት እንደሚገባ፤ ጸጋዎችን እና አቅሞችን በመለየት ባለሃብቶች የሚሻሙትን ዘርፍ ለወጣቱ ተጠቃሚነት ማዋል፤ የአገናኞችን ብልሹ አሠራር መከታተል እና ግንባታቸው የተጓተቱ ኮሌጆችን ማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሠሩም አሳስበዋል።
ከማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አኳያም ተቋሙ ተጠናክሮ የምጣኔ ሃብት ማዕከል እንዲኾን እየተሠራ መኾኑን፣ የሥነ ምድር ጥናት መሠራቱ፣ ማዕድን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን አፈላልጎ ለማስተሳሰር መሞከሩን ጠቅሰው በጥንካሬ ገልጸዋል።
በውስንነት እና እንዲተኮርበት ካነሷቸው ሀሳቦች መካከልም በዘርፉ ተሰማርተው ግን የጊዜ ገደባቸው ያለፈባቸው እና የማይሠሩት ክትትል እንዲደረግ፣ ለክልሉ ወሳኝ በኾኑ የተመረጡ እና የተቆጠሩ ማዕድናት ጥናት፣ ፍለጋ እና ማውጣት ላይ ተተኩሮ ቢሠራ የሚል ሃሳብ ተነስቷል።
የዕውቀት እና ክህሎት ልማት ላይም ተሞክሮ በመቅሰም በትኩረት ቢሠራ እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ መፍታት እንዲቻል አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን