
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን እና የሚደግፋቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ዛሬም እየገመገመ ነው።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው የበጀት ዓመቱን የተቋሙ እቅድ አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።
በበጀት ዓመቱ ለፍትሕ ሥርዓቱ የሚመጥን ፍርድ ቤቶችን መገንባት እና ለሥራ ምቹ ማድረግ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈ በዞኖች ጭምር እየተከናወነ መኾኑን ገልጸዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጀመረውን ኮሪደር ልማት የሚደግፍ ጭምር መኾኑም ነው የገለጹት።
የማኅበረሰቡን አገልግሎት አሠጣጥ ለማዘመን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የመጀመሪያ ምዕራፍ የዲጅታላይዜሽን ሥራ መሥራት መቻሉን ገልጸዋል።
የፍትሕ ሥርዓቱን ቅልጥፍና ለማሳደግ ባሕላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን እና አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶችን የማጠናከር ሥራ መሥራቱንም አቅርበዋል።
የዳኝነት ነጻነት፣ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ለማጠናከር የዳኞች ያለመከሰስ አዋጅ እንዲጸድቅ ተደርጓል። ግልጽ ችሎት ማደራጀት እና የሕግ እና የአሠራር ማዕቀፎችን ማስተካከል ተችሏል ብለዋል።
በወንጀል ለተከሰሱ እና ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ 2 ሺህ 777 ተከሳሾች ነጻ የሕግ ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል። ከእነዚህ ውስጥ በ606 መዛግብት 771 ተከሳሾች ጉዳይ ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በ1 ሺህ 425 መዝገቦች ውስጥ የሚገኙ 2 ሺህ 6 የሚኾኑት ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!