የመምህራንን አቅም ለማጎልበት እየተሠራ ነው።

18

ጎንደር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በጎንደር ከተማ ለመካከለኛ ደረጃ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ሥልጠና አስጀምሯል። ሥልጠናው ሁሉንም የጎንደር ዞኖች ያካተተ ነው።

‎የአቅም ግንባታ ሥልጠናው ከ2ሺህ 500 በላይ ሠልጣኞችን እንደሚያካትት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ስንታየሁ ነጋሽ ተናግረዋል።

የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናው ተግባር ተኮር መኾኑ የተገለጸ ሲኾን የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ እንደሚያስችል አብራርተዋል።

‎አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ እየተተገበረ መኾኑን ያነሱት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ክንዱ ዘውዱ ከሙያ ጋር የሚያስተዋውቅ እና አቅምን የሚያጎለብት ሥልጠና በመኾኑ ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተገቢው መንገድ ለመተዋወቅ ያግዛል ብለዋል።

‎ሥልጠናው የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያጎለብት፣ መምህራን ተማሪዎችን በተሻለ መንገድ እንዲመሩ የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር መምህራን ኮሌጅ የሥነ ትምህርት ክፍል ኀላፊ አሠልጣኝ መምህር ተስፋ ዋለ ናቸው።

‎የችግር መፍቻ ቁልፉ ትምህርት ነው ያሉት የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ የመምህራንን አቅም ለማጎልበት በሚደረገው ጥረት ከተማ አሥተዳደሩ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ሥልጠናው ክፍተቶቻችንን የምንሞላበት ነው የሚሉት ሠልጣኝ መምህራኑ ከሥልጠናው በኋላ ወደ ትምህርት ቤታቸው በመመለስ ያገኙትን ልምድ ከነበራቸው ችሎታ ጋር በማዛመድ በተግባር እንደሚጠቀሙበት ገልጸዋል።

‎በሦስት የማሠልጠኛ ጣቢያዎች የሚከናወነው የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናው ለ13 ቀናት እንደሚቆይም ተገልጿል።

ዘጋቢ:- ተስፋዬ ጋሹ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!


Previous articleትውልድን በማነፅ ሀገርን ለማሻገር የመምህራን ሚና የላቀ ነው።
Next articleየፍርድ ቤቶችን አገልግሎት አሠጣጥ ለማዘመን እየተሠራ ነው።