ትውልድን በማነፅ ሀገርን ለማሻገር የመምህራን ሚና የላቀ ነው።

6

ከሚሴ: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት ለመካከለኛ ደረጃ መምህራን፣ ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ልዩ የክረምት አቅም ግንባታ ሥልጠና በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ተጀምሯል።

በሥልጠናው ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሁሉም ወረዳ እና ከተማ አሥተዳደር የተውጣጡ መካከለኛ መምህራን እና ርእሳነ መምህራን ተሳትፈዋል።

በሥልጠናው የተሳተፉ መምህራን ለአሚኮ በሰጡት አስተያየት ሥልጠናው ያላቸውን አቅም የሚያጎለብት ይኾናል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ከሊል ሐሰን ሥልጠናው ለመካከለኛ መምህራን እና ለትምህርት አመራሮች መሰጠቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራን የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እንድሪስ አሕመድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሥልጠናው መሰጠቱ በትምህርት ዘርፉ አጋጥሞ የነበረውን የትምህርት ዘርፍ ስብራት ለመጠገን እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች ከሥልጠናው በኋላ በመጡበት ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንዲሠሩ ይጠበቃልም ብለዋል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ በበኩላቸው ትውልድን በማነጽ ሀገርን ለማሻገር የመምህራን ሚና የላቀ መኾኑን ጠቅሰው መምህራን በሥልጠናው በሚያገኙት እውቀት ለትምህርት ጥራት በትጋት እንዲሠሩ አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየትምህርት ስብራትን ለመጠገን የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ ነው።
Next articleየመምህራንን አቅም ለማጎልበት እየተሠራ ነው።