የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ ነው።

6

ደብረ ማርቆስ: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመካከለኛ ደረጃ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና ርእሳነ መምህራን ሥልጠና በደብረ ማርቆስ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተጀምሯል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር መምህራን በተመደቡበት የሥልጠና ቦታ በመገኘት ሥልጠናቸውን መከታተል ጀምረዋል።

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመሥገን ሥልጠናው የመምህራንን አቅም እና ክፍተት የሚሞላ በመኾኑ ሥልጠናውን በሚገባ በመውሰድ ችግር ፈች እና ለሥርዓተ ትምህርቱ መሳካት የበኩላችሁን ድርሻ ልትወጡ ይገባል ብለዋል፡፡ የትምህርት ሥርዓትን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ የሥልጠናው ግብ መኾኑን ተናግረዋል።

የደብረ ማርቆስ መምህራን ኮሌጅ ዲን ዜና ገብረማርያም በበኩላቸው አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ያደረገ ሥልጠና በመኾኑ በቆይታችሁ የሚፈለገውን እውቀት እና ክህሎት መጨበጥ ይገባል ብለዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ምክትል ኀላፊ ደመላሽ ታደሰ በግጭቱ ምክንያት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሥራ ለማስጀመር እና ወደ ተሻለ የሥራ መንፈስ ለመግባት ተጨማሪ ግብዓት የሚገኝበት እና የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለመለወጥ አጋዥ በመኾኑ ሥልጠናውን በንቃት እና በትጋት መከታተል ይገባል ነው ያሉት።

በምሥራቅ ጎጃም ዞን በግጭቱ ምክንያት ከ800 በላይ ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማር ሥራቸው እንዳልገቡ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleስለ ከውል ውጭ የጉዳት ካሳ ምን ያውቃሉ?
Next articleትውልድን በማነፅ ሀገርን ለማሻገር የመምህራን ሚና የላቀ ነው።