አዲሱ የመሬት ካሳ ክፍያ መመሪያ ጸድቆ ወደ ተግባር አለመግባት በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እና ተቋማት ገለፁ፡፡

1278

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ደግሞ መመሪያው በፌዴራል ደረጃ ባለፈው ሳምንት መጽደቁንና በቅርቡ ሥራ ላይ እንደሚውል ገልጿል፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሻሽሎ ይወጣል የተባለው አዲሱ የመሬት ካሳ ክፍያ መመሪያ መዘግዬቱ በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ መስተጓገል እንደ ፈጠረ በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች እና ከተሞች ተዘዋውረን ያነጋርናቸው ባለሀብቶችና ተቋማት አስታውቀዋል፡፡

አቶ በእሱፍቃድ ተስፋዬ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ሪል እስቴት ዘርፍ ለመሰማራት ፕሮጀክታቸውን ያቀረቡበት ጊዜ ከአንድ ዓመት ማለፉን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የመሬት ካሳ ክፍያ መመሪያ ጸድቆ በአለመደረሱ ደግሞ የሚገባውን የመሬት ካሳ ከፍሎ ወደ ሥራ ለመግባት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ነው የተናገሩት፡፡ በሥራ መዋል የሚችለውን ገንዘብ በአግባቡ እንዳይጠቀሙ መሰናክል መፍጠሩንም ነው የገለፁት፡፡ ለሪል ስቴት ግንባታ እስከ 200 ሚሊዮን ብር መድበው የካሳ ክፍያ መመሪያ እስከሚመጣ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም ፈለቀ ደግሞ አቶ በእሱፍቃድ የሰጡትን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡ በተለይም ወደ ከተማ ክልል የገቡትን የኢንቨስትመንት መሬቶች ጨምሮ በአጠቃላይ 263 ሄክታር መሬትን የመሬት ካሳ መመሪያ በመዘግየቱ ለባለሀብቶች ማስተላለፍ እንዳልቻሉ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወረዳው በአግባቡ እንዳይለማ እና ለበርከታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር መድረጉን አብራርተዋል፡፡

በሀገረ ማርያም ከሰም ወረዳ የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት የኢንዱስትሪ ዞን ባለሙያ አቶ መንግሥቱ ከተማ ደግሞ የመሬት ካሳ መመሪያው ጸድቆ ባለመድረሱ በወረዳው በአዲስ መስፈርቶችን አሟልተው ለተመለሙሉ 44 ፕሮጀክቶች መሬት መስጠት እንዳላስቻለ ገልፀዋል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ደግሞ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ እና ለ1 ሺህ 91 ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዕቅድ ያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የመሬት የካሳ ክፍያ መመሪያ ጸድቆ ወደ ወረዳዎች መውረድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ተፈራ ወንድማገኝ እንደገለጹት ደግሞ የመሬት ካሳ አዋጅ በባለፈው ዓርብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ እንደወጣ አስተውቀዋል፡፡ ‘‘አሁን ከተማ ልማት ሚኒስቴር የተሰጡ አስተያዬቶችን አካትቶ በነጋሪት ጋዜጣ ማውጣት ነው የቀረው፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ የአንድ ተቋም ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ መመሪያው ወደ ክልል ሲደርስ ደግሞ እንደ ክልሉ ነባራዊ ሁኔታ በመውሰድ ሥራ ላይ ይውላል’’ ብለዋል፡፡ የመሬት ካሳ ክፍያ መመሪያ ጸድቆ ባለመውጣቱ ደግሞ በተያዘው በጀት ዓመት ከአርሶ አደር መሬት ተወስዶ ለባለሀብት መስጠት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አዳሙ ሺባባው

Previous articleበዚህ ክረምት አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ያለመው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ዛሬ ይጀመራል፡፡
Next articleየአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ተጀመረ፡፡