
ገንዳውኃ: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017/18 በመኸር የእርሻ ወቅት በዘር ለመሸፈን ከታቀደው የአኩሪ አተር ዘር እስካሁን 137 ሺህ 621 ሄክታር በዘር መሸፈኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና ግብርና መምሪያ ኀላፊ አንዳርጌ ጌጡ ተናግረዋል። ከዚህም ውስጥ ከ81 ሺህ 500 ሄክታር በላይ የሚኾነው በኩታ ገጠም የተሸፈነ መኾኑን አስረድተዋል።
295 ኩንታል ምርጥ ዘር በባለሙያ መሠራጨቱን ተናግረዋል። 947 ኩንታል የሚኾነው ዘር ደግሞ በአርሶ አደሮች የአካባቢ ዘር ተመርጦ የተዘራ ነው ብለዋል።
በምርት ዘመኑም ከ4 ሚሊዮን 305 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ኀላፊው ያስረዱት።
የአኩሪ አተር የዘር ሽፋን በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱንም አስታውቀዋል። 80 በመቶ የሚኾነው ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውል መኾኑንም አስገንዝበዋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግም ከምርጥ ዘር እና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት አቅርቦት በተጨማሪ አልሚዎች በሜካናይዜሽን እና በኩታ ገጠም እንዲያለሙም በትኩረት እየተሠራ እንደኾነ አብራርተዋል።
አርሶ አደሮች የባለሙያ ምክረ ሀሳብ በመውሰድ እና ባለሙያዎች ታች ድረስ ወርደው ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ምርት እንዲያገኙም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ በምድረ ገነት ዙሪያ የሚገኘው የኮርደም የእርሻ ልማትና የዋሊያ አንገት የእርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ ዓለሙ ሙላው 400 ሄክታር በዘር ለመሸፈን አቅደው 300 ሄክታር መሬት በአኩሪ አተር ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
ከአንድ ሄክታርም ከ24 እስከ 28 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
እያለሙት ካለው ሰብል ከ7 ሺህ 800 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት አቅደው እየሠሩ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በቋራ ወረዳ የገለጎ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብሬ ተባባል ከሚያለሙት 6 ሄክታር መሬት 5 ሄክታር የሚኾነውን በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈናቸውን ተናግረዋል።
አልሚዎች የሚጠብቁትን ምርት ለማግኘት የምርጥ ዘር፣ ማሳን የማንጣፈፍ ሥራ እና በቂ የአፈር ማዳበሪያ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት ከ3 ሚሊዮን 76 ሺህ ኩንታል በላይ የአኩሪ አተር ምርት መገኘቱም ተመላክቷል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!