መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።

22

አዲስ አበባ: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመተባበር የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራን በኦሮሚያ ክልል አስጀምረዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ማከናወን ተገቢ መኾኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

በከተማ እና ገጠራማ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ለመቀየር መንግሥት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን አንስተዋል።

ሚኒስትሯ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሰበታ ሀዋስ ወረዳ የነዋሪዎች ሞዴል መንደር፣ የትምህርት ቤት እና መጸዳጃ ቤት ግንባታ አስጀምረዋል።

በዚህ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ 3 ሺህ ለሚኾኑ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

መሥሪያ ቤቱ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች እያከናወነ መኾኑንም ጠቁመዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ፈንታ ደጀን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ቤት በመገንባት እና በማደስ የኑሮ ዘይቤያቸው እንዲሻሻል ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ሕይወት ከመታደግ ባሻገር ችግኝ በመትከል እንደሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ምኅዳራዊ ጠቀሜታን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት የተተከሉ ችግኞች የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ፣ የአፈር ለምነትን በመጨመር፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ሚናቸው የጎላ መኾኑንም ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተጠይቋል።

ዘጋቢ:- ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዜጎች በንጹሕ አካባቢ የመኖር መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው።
Next articleበመኸር የእርሻ ወቅት ከ137 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በአኩሪ አተር መሸፈኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን አስታወቀ።