የዜጎች በንጹሕ አካባቢ የመኖር መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው።

16

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል እናድርግ” በሚል መሪ መልዕክት በመላው ሀገሪቱ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው። የዚሁ ንቅናቄ አንድ አካል የኾነ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ክትትል እና ቁጥጥር ባለሙያ
አበበ ሞላ የሰው ጤና እና የአካባቢ ጤናን መጠበቅ ትልቅ ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። የሰው ጤናን እና የአካባቢ ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሕጎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
የአፈር፣ የውኃ፣ የአየር እና የድምጽ ብክለቶች አሉ ያሉት ባለሙያው አካባቢን እና ሰውን ከእነዚህ የብክለት አይነቶች መጠበቅ ግድ እንደሚል ተናግረዋል። እነዚህ ብክለቶች ሲጠበቁ ጤናማ ማኅበረሰብ ይፈጠራል ነው ያሉት። የማኅበረሰብ ጤና መታወክ በብዛት የሚነሳው ከአካባቢ ብክለት መኾኑንም ገልጸዋል።
ለአብነት ሙያዊ ያልኾነ የፕላስቲክ አወጋገድ የማኅበረሰብን ጤና እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት። የአካባቢ ጤና ካልተጠበቀ የሰው ልጅ ጤንነት እንደማይጠበቅም አመላክተዋል።
አካባቢን የመጠበቅ ግንዛቤ እያደገ መጥቷል ያሉት ባለሙያው ነገር ግን አሁንም በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ነው ያሉት። የድምጽ ብክለት በርካታ ወገኖችን እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት። የድምጽ ብክለት አይደለም ሰውን ሕንጻን የመሰነጣጠቅ ትልቅ ኃይል እንዳለው ነው የገለጹት።
የማሰባሰብ ጤንነትን ለመጠበቅ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መኾናቸውንም ተናግረዋል። ደኖችን መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። አካባቢን የመጠበቅ እና የመንከባከብ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የአካባቢ ጥበቃ በአንድ ተቋም ብቻ አይሠራም ያሉት ባለሙያው የቆሻሻ አያያዝን ዘመናዊ ማድረግ የሠለጠነ ማኅበረሰብ መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ ዳይሬክተር አወቀ ይታይ “ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል እናደርግ” ንቅናቄ በአማራ ክልል እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል።
ጽዱ አካባቢን እውን የማድረግ ሂደቱ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል። የፕላስቲክ፣ የአፈር፣ የአየር እና የድምጽ ብክለትን ለመከላከል እንደሚሠራ ተናግረዋል።
ሥራዎቹ ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገባቸው እንደሚሠሩም ገልጸዋል። ጽዱ ኢትዮጵያን እውን ማድረግ በርካታ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣ ተናግረዋል።
ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል እናድርግ የሚለውን ንቅናቄ ውጤታማ እንዲኾን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ኀላፊ በልስቲ ፈጠነ የጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል ማድረግ አንዱ አካል የኾነ ችግኝ መተከላቸውን ገልጸዋል። ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተደረገው የመጀመሪያው ንቅናቄ በከፍተኛ ደረጃ የፕላስቲክ ማስወገድ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ፕላስቲኮችን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ምክትል ኀላፊው ይህም አካባቢን ጽዱ ከማድረግ ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።
ወጣቶች ፕላስቲኮችን እየሰበሰቡ ፕላስቲኮችን መልሰው ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ድርጅቶች እያስረከቡ መኾኑን ገልጸዋል። በፕላስቲክ ላይ የተሠራው ሥራ ትልቅ ለውጥ እንደታየበትም ተናግረዋል። ጽዱ ከባቢን የመፍጠር እና አካባቢን በአረንጓዴ የማስዋብ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
ፕላስቲክ ለረጅም ጊዜ ሳይበሰብስ ስለሚቆይ አካባቢን እንደሚጎዳ ተናግረዋል። አሁን ላይ ፕላስቲክ ጥቅም ላይ እንዳይውል ሕግ መውጣቱን እና ያን ለማስቆም እንደሚሠራ ገልጸዋል። ዜጎች የወረቀት እና የጨርቅ መያዣዎችን እንዲጠቀሙም አሳስበዋል።
ማኅበረሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ባሕሉን እንዲያዘምንም አስገንዝበዋል። ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር የእያንዳንዱ ሰው ሥራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተሾመ አቡኔ የዜጎች በንጹሕ አካባቢ የመኖር መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው ብለዋል።
ዜጎች በንጹሕ አካባቢ እንዲኖሩ ደግሞ ንጽሕናን ባሕል ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። አካባቢን ውብ እና ጽዱ ማድረግ ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። ዜጎች በጽዱ አካባቢ እንዲኖሩ ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል የማድረግ ንቅናቄ እየተተገበረ መኾኑን ገልጸዋል።
በተለይ የፕላስቲክ አጠቃቀም ዜጎችን እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት። የፕላስቲክ አያያዝ ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የፕላስቲክ አጠቃቀም ሕግ እንዳለም ተናግረዋል።
ሕጉን በአግባቡ በማይተገብሩ አካላት ላይ በሕግ አግባብ መጠየቅ እንደሚገባ ገልጸዋል። መልካም ሥራ የሠሩትን ደግሞ መሸለም ይገባል ነው ያሉት።
ጽዱ ኢትዮጵያን ባሕል የማድረግ ንቅናቄ ለስድስት ወራት እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ሀገራት ጽዱ አካባቢን ፈጥረዋል፣ እኛም በቅንጅት ከሠራን ጽዱ ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን ነው ያሉት።
ባለፉት ስድስት ወራት ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተፈጠረው ንቅናቄ ትልቅ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። ሕዝቡ ብክለት ይቁም የሚል ግንዛቤው ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመንግሥት የልማት ድርጅቶች እያሳዩ ያለው ተጨባጭ ለውጥ አበረታች ነው።
Next articleመንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው።