
ደሴ: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት ለመካከለኛ ደረጃ መምህራን፣ ምክትል ርእሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች የሚሰጠው ልዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በደሴ ከተማ ተጀምሯል፡፡
በሥልጠናው ከደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደሮች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
ለሠልጣኞች በበይነ መረብ መልእክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) “የመምህራንን እና የትምህርት መሪዎችን አቅም ማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ አለው” ብለዋል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱን በተገቢው የተረዱ መምህራን እና የትምህርት መሪዎችን መፍጠር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ተቀራራቢ ግንዛቤ በመያዝ ትውልዱን በዕውቀት እና በመልካም ሥነ ምግባር ለመገንባት በጋራ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ዓለምነው አበራ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል መምህራን የላቀ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡ የሥልጠናው ቀዳሚ ግብ የትምህርት ጥራትን በማሻሻል የተማሪዎችን ውጤት ከፍ ማድረግ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው ሠልጣኞች እንደገለጹት ሥልጠናው አቅማችንን በማሳደግ የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ሥልጠናው ለሁለት ሳምንት እንደሚቆይ የወጣው መርሐ ግብሩ ይጠቁማል።
ዘጋቢ:- ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
