
ፍኖተ ሰላም: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና መሪዎች የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና በፍኖተ ሰላም ከተማ እየተሰጠ ነው።
በሥልጠናው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ በእውቀት፣ በአመለካከት፣ በክህሎት እና በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ ትውልድ ለመገንባት የመምህራን ሚና የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ መምህራን የራሳቸውን አቅም በማጎልበት የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር መሥራት ይገባል ብለዋል።
በተለይም በሰላም እጦቱ የተቋረጠው መማር ማስተማር እንዲቀጥልም መምህራን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሥልጠናው በመማር ማስተማሩ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የይዘት፣ የማስተማር ሥነ ዘዴ እና ሌሎች ዘርፎች ያካተተ መኾኑን የምዕራብ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ የስጋት ደሴ ገልጸዋል።
መምህራንን እና የትምህርት ቤት መሪዎችን ተወዳዳሪ እና ከዘመኑ ቴክኖሎጅ ጋር መራመድ እንዲችሉ በማድረግ ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ አላማ ያደረገ ነው ብለዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በመምህራን ላይ የብቃት እና የአቅም ማነስ ችግሮች በመስተዋላቸው ትውልዱ ላይ ከፍተኛ ስብራት እንዲፈጠር ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
መምህራን አሁን የሚሰጠው ሥርዓተ ትምህርት የሚጠይቀውን ብቃት እና የትምህርት አሰጣጥ ማሟላት ባለመቻላቸው መማር ማስተማሩ ላይ ተግዳሮት ፈጥሯል ብለዋል።
በአቅም እና ባሕሪ የተሻለ ትውልድ ለመቅረጽ መምህራን የራሳቸውን አቅም በየጊዜው በማሻሻል አስፈላጊ የኾነ እውቀት መስጠት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በሥልጠናው በምዕራብ ጎጃም ዞን ከሚገኙ ከ500 በላይ የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና መሪዎች ይሳተፋሉ።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
