የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እያሳዩ ያለው ተጨባጭ ለውጥ አበረታች ነው።

25

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የልኅቀት ዲዛይንና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን፣ ዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ የአማራ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኢንተርፕራይዝ፣ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ኀብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት የቀረቡ ሪፖርቶችን መሰረት በማድረግ ላቀረቧቸው ጥያቄዎች በልማት ድርጅቶቹ የሥራ ኀላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት የፕሮጀክት አፈጻጸም ዝቅተኛነት የተነሳ ሲኾን በዕቅድ ተይዘው በጸጥታ ችግር ምክንያት አለመሠራቱ እና ሥራ በተጀመረባቸውም ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም አስቸጋሪ መኾኑን በምክኒያት ተነስቷል።

የሠራተኛ አያያዝ በተመለከተ አብዛኛው ሠራተኛ በትጋት የሚሠራ ኾኖ ችግር ያለበትን ሰው ለማረም በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑም ተነስቷል። ያለአግባብ ተጠቃሚነቶችን ለማረም ሕጉን ተከትሎ በመሥራት ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ኅላፊዎቹ አንስተዋል።

የፕሮጀክቶች ገንዘብ አከፋፈል ሥርዓትን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ተቋማት የተጓዙበትን ርቀት ለቋሚ ኮሚቴ አባላት አስረድተዋል፡፡ ማኅበራዊ ኀላፊነቶችን ከመወጣት አንጻር ፕሮጀክቶች ባሉባቸው አካባቢዎች የተከናወኑ ተግባራትን በተለይም የትምህርት ቤቶችን ግንባታ አብራተዋል፡፡

የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሃናን አብዱ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባላቸው አፈጻጸም የታዩ ጠንካራ ጎኖችን እና መሻሻል የሚገባቸውን ደካማ ጎኖች አብራርተዋል፡፡

የልማት ድርጅቶች ሪፖርት ያቀረቡ አምስት ተቋማትን ጨምሮ 12 የልማት ድርጅቶችን ያካተተ ነው፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለዕቅድ እና ትግበራ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ አሠራር እና ማሻሻያዎችን እያደረጉ ነው፣ ይህም ሊበረታታ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጅ አጠቃቀማቸውን በማሻሻል እያሳዩ ያለው ተጨባጭ ለውጥ አበረታች መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ከኪሳራ ወደ ትርፋማና ውጤታማ አሠራር ለመግባት መሪው እና ባለሙያው ያሳየው ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ አዳዲስ መመሪያዎችን እና አሠራሮችን በመዘርጋት የኪሳራ አካሄድን ለመቀልበስ ገቢ የማሰባሰብ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉ የሚበረታታ ተግባር መኾኑን ገልጸዋል፡፡

የትኩረት ማዕከል የኾኑ ሥራዎችን እና ፕሮጀክቶችን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲሠሩ እና እንዲተገበሩ አልተደረገም ሊሻሻል ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይም በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ርብርብ በማድረግ በኩል ያሉ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

የኅብረተሰቡን ባለቤትነት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንዲሠሩ የተቀመጠውን አቅጣጫ መተግበር እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የክልሉን ኅብረተሰብ ቁልፍ የልማት ችግሮች የሚፈቱ ማዕከላት በመኾናቸው ለደንበኞቻቸው ፈጣን እና ፍትሐዊ አገልግሎት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡

የኦዲት ግኝት ክፍተቶችን በማረም የሃብት ብክነትን መከላከል እና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመምህራንን አቅም ማሳደግ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጉልህ አበርክቶ አለው።
Next articleየዜጎች በንጹሕ አካባቢ የመኖር መብት ሕገ መንግሥታዊ ነው።