
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም (አብመድ) የዚህ ዓመት የአረንጓዴ አሻራ ቀን ዛሬ ዓርብ ግንቦት 28/2012 ዓ.ም ይጀመራል፡፡
መርሀ ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሀዋሳ ላይ ይጀመራል። በአማራ ክልል ደግሞ በሰሜን ሜጫ ወረዳ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ ያስጀምራሉ። በሌሎች ክልሎችም ዛሬ መርሀ ግብሩ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 22/2011ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ ቀን 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በመትከል አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው፡፡
በክብረ ወሰንነት ተይዞ ከነበረው ከአምስት እጥፍ በላይ መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በህንድ ተይዞ የነበረውን በአንድ ጀምበር በ800 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ከ50 ሚሊዮን በላይ ችግኝ የመትከል ክብረ ወሰን ኢትዮጵያ በብዙ ርቀት አሻሽላዋለች፡፡
ዘንድሮ ደግሞ በክረምት ወቅቱ በሚኖረው የአረንጓዴ አሻራ ወቅት 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ነው የታቀደው፡፡