
ደብረ ብርሃን: 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሸዋ ዞን እና ደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለመካከለኛ ደረጃ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች የሚሰጥ ልዩ የክረምት አቅም ግንባታ ሥልጠና በደብረ ብርሃን ከተማ ተጀምሯል።
በምክትል ርእስ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) በበይነ መረብ አማካኝነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በእውቀት የዳበረ እና ችግሮቹን በሠለጠነ መንገድ የሚፈታ ማኅበረሰብ ለመገንባት ትምህርት ቀዳሚው መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት የትምህርት ዘርፍ የተማረ ኃይል መጋቢ ኾኖ ተልዕኮውን ማሳለጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ለዚህ ተግባር መሳካት ደግሞ ትምህርትን ማዘመን እና እውቀትን ማሻሻል አስፋላጊ መኾኑን አንስተዋል።
መምህራን ራሳቸውን ብቁ ማድረግ እና በእውቀት የሚያምኑ ተማሪዎችን ለማፍራት መትጋት እንዳለባቸው ዶክተር ሙሉነሽ ተናግረዋል፡፡ ትምህርት ከሁሉም የፖለቲካ ጉዳይ የጸዳ በመኾኑ ስለሰላም መምህራን ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ጸጋዬ እንግዳወርቅ የመምህርነት ሙያ የማስተማር ብቻ ሳይኾን የመማር አቅምን ለማሳደግ ዕድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ሥልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ተጨማሪ እውቀት በመጨበጥ በትምህርት ጥራት ላይ እሴት ለመጨመር ሠልጣኞች መዘጋጀት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ ሥርዓተ ትምህርቱን ያማከለ ሥልጠና አስፈላጊ በመኾኑ አዳዲስ የተቀረጹ የትምህርት መስኮችን ከግምት ውስጥ ያስገባውን ሥልጠና በመኾኑ በአግባቡ መከታተል እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል ገጠር መንገድ ምክትል ኀላፊ አስራቴ አለኸኝ በውስብስብ ችግር ውስጥ እያለፈ የሚገኘው የትምህርት ዘርፍ ቀዳሚ ተዋናይ ኾነው ተግባሩን እያከናወኑ ያሉ መምህራን መደገፍ አለባቸው ብለዋል፡፡
ከነዚህ የድጋፍ ማዕቀፎች መካከል አንዱ ሥልጠና በመኾኑ መምህራን ራሳቸውን አብቅተው የተሻለ እውቀት እና ክህሎት ያለው ትውልድ ለማፍራት በቁጭት መንቀሳቀስ እንዳላባቸው አሳስበዋል።
ከዞኑ እና ከተማ አሥተዳደሩ የተውጣጡ 2 ሺህ 900 በላይ የሚኾኑ መምህራን ለ13 ተከታታይ ቀናት ሥልጠናውን የሚወስዱ ይኾናል ተብሏል።
ዘጋቢ:- ስንታየሁ ኃይሉ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
