የክልሉን ኢኮኖሚ የሚደግፉ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርቷል፡፡

8

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

አፈጻጸማቸው ከተገመገሙ ተቋማት መካከል የልኅቀት ዲዛይን እና ቁጥጥር ኮርፖሬሽን አንዱ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አብርሃም አያሌው ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት ከ146 ሚሊዮን ብር በላይ ግብዓት በግዥ ማሟላት ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የተቋሙን አሠራር በቴክኖሎጅ የመደገፍ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር እና መመሪያዎችን የማሻሻል ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል፡፡ የፋይናንስ እና ሰው ኃይል አሥተዳደር ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

የፊዚካል እና የአሥተዳደር ሥራዎችም ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ ኾነዋል፤ ይህም ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም አጋዥ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ለመሪውም ኾነ ለሠራተኛው ሥራውን እና በተቋሙ ውስጥ ያሉ ንብረቶችን መቆጣጠር እንዳስቻለም አንስተዋል፡፡

የፊዚካል ሥረራዎችን አአፈጻጸም በተመለከተ በበጀት ዓመቱ 330 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ ቆይተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 101 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹም የትራንስፖርት እና መሠረተ ልማት፣ የሕንጸ እና ከተማ ልማት፣ የውኃ መስኖ ፕሮጀክቶች እንደኾኑ ነው የገለጹት፡፡

ኮርፖሬሽኑ በምርምርና ምህንድስና ዘርፉ በላቡራቶሪ ማዕከሉ የናሙና ፍተሻ ሥራዎች መሥራቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከውዝፍ እና በበጀት ዓመቱ ከተሠሩ ሥራዎች 508 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። 73 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትረርፍ መገኘቱ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡ አብዛኞቹ የመንግሥት ተቋማት ላይ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው በኪሰራ አየተሠሩ ያሉ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡ ለተግባራት አፈጻጸም የሥራ አመራር ቦርዱ የተሻለ ድጋፍ እና ክትትል ማደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ሌላው የዘመን ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሥራ አሥፈጻሚ ታደሰ ግርማ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፡፡ በሪፖርታቸውም በዝግጅት መርሐ ግብር ሠራተኞችን የማብቃት፣ ተሽከርካሪዎችን እና ማሽነሪዎችን የመጠገን ሥራዎች መሠራቱን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱም 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ነው ያሉት። 31 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ መገኘቱን አንስተዋል፡፡ የቆዩ እና አክሳሪ ፕሮጀክቶችን የዋጋ ማሻሻያ እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ ለ20 ሺህ 377 ዜጎች በቋሚ እና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡ የተቋሙን አደረጃጀት ስያሜ እና የንግድ ምልክት ሪፎርም የማድረግ ሥራ በውጤታማነት መጠናቀቁንም አብራርተዋል፡፡ ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመወጣት በኩል የትምህርት ቁሳቁስ ለተማሪዎች እና ለአቅመ ደካሞች የቤት ጥገና ሥራዎች ላይ ተቋሙ መሳተፉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ሥራዎችን በጥራት እየሠራ ቢኾንም የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ሥራዎቹን ለመሥራት ተግዳሮት እንደፈጠሩበት ነው ያስገነዘቡት፡፡ የዋጋ መሻሻያ ለሚያስፈልጋቸው ፕሮጀክቶች ማሻሻያ መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ዘላለም በላይ የተቋሙን የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል፡፡

ተቋሙ የሥራ ማስኬጃ በጀት ያልተበጀተለት በመኾኑ በራሱ እንዲንቀሳቀስ እና ወጭውን ሸፍኖ ለመሥራት ታቅዶ ሢሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ እንዲመጣ አደራ የተጣለበት በመኾኑ የሚሠሩ የነበሩ ጥቃቅን ተግባራትን ከፍ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በ11 ወሩ 347 ሚሊዮን ብር ገቢ ማገኘቱን እና ከዚህም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንደተገኘም ነው የጠቆሙት፡፡ ኢንተርፕራይዙ 5 ቢሊዮን ጥቅል ሃብት አንዳለውም አሳውቀዋል፡፡ የምርት ሥራዎችን አፈጻጸም በሚመለከት በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ባለመገባቱ የምርታማነት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደኾነም ነው ያስረዱት፡፡ በብየዳ እና መገጣጠም ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሢሠራ መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሼዶችን አንስተዋል፡፡

የኢንቨስትመንት ሥራዎች አለመጠናቀቅ፣ የውል ጊዜያቸው ለዓመታት የዘገዩ ሥራዎች ኢንተርፕራይዙን ለተጨማሪ ወጭ እየዳረጉት መኾኑ ነው በሪፖርቱ የተመላከተው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከመንገድ ቢሮ ጋር ችግር ፈቺ የኾኑ የተንጠልጣይ ድልይ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ለኮሪደር ልማት ሥራዎች ስማርት ፖል በመሥራት ለሥራው ጥራት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውል ይዞ ለመሥራት ዕድል እንደፈጠረላቸውም በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የተጀመረውን የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ መጨረስ፣ የወኪንግ ትራክተር ሞዴልን በማስፋፋት ከግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በሰፊው ለማምረት አቅጣጫ አስቀምጠው እየሠሩ እንደሚገኙም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በኢንተርፕራይዙ የሚመረቱ ምርቶችን የክልሉ ተቋማት መጠቀም እንዲችሉ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ቢዘጋጅ ለሥራቸው አጋዥ እንደሚኾንም ነው የተናገሩት፡፡

ዘጋቢ፦ ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራ እና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
Next articleበበጀት ዓመቱ ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ከሙስናና ብልሹ አሠራር ማዳን ተችሏል።