ለ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራ እና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።

22

ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ምክር ቤት የከተማ፣ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ያቀረቡት የሥራ እና ሥልጠና ቢሮ ኀላፊ ስቡህ ገበያው (ዶ.ር) የዲጂታላይዜሽን ልማት በ235 ኮሌጆች መጀመሩን ገልጸዋል።

ለወጣቶች ስለ ሥራ ፈጠራ ሥልጠና መሰጠቱን እና ለ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል። የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ውስጥም 981 ሺህ 751 ቋሚ መኾኑ ተገልጿል። 1 ሺህ 925 ሼዶች በ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መሠራታቸውንም ዶክተር ስቡህ ጠቅሰዋል።

ለ202 ሺህ ኢንተርፕራይዞች እና አንቀሳቃሾች የ7 ቢሊየን 588 ሚሊየን ብር የገበያ ትስስር መፈጠሩንም ዶክተር ገበያው ጠቅሰዋል።

የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሠልጣኞችን ተቀብሎ የማሠልጠን እቅድ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት አነስተኛ አፈጻጸም መኖሩን በውስንነት አንስተዋል።

የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ አበባ ጌታሁን ባቀረቡት ሪፖርት ቢሯቸው በተቋም ግንባታ፣ ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የቢሮ እድሳት ማከናወኑን ገልጸዋል።

የማዕድን ጥናት እንዲሁም 4 አዲስ እና 2 ነባር የሥነ ምድር ጥናት ፕሮጀክቶች ማዕድናት መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

ከክልሉ ውስጥ 45 ሺህ 525 ካሬ ኪሎ ሜትር የሥነ ምድር ጥናት መደረጉን ገልጸዋል። በዚህም የማዕድናትን ሥርጭት መረጃ ለማወቅ መቻሉን ተናግረዋል።

በጥናቱ የደንጋይ ከሰል፣ ኮፐር፣ ብረት ነክ የግንባታ እና ሌሎችም ማዕድናት መገኘታቸውንም ገልጸዋል።

በ265 የማዕድን ምርመራ እና የምርት ፈቃድ መሰጠቱን እና በተለያዩ ደረጃዎች ለሚገኙ አምራቾች ፈቃድ መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

ለ4 ሺህ 136 ኢንተርፕራይዞች በማዕድን ዘርፍ ፈቃድ መሰጠቱን እና ለ45 ሺህ 136 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ወይዘሮ አበባ አመላክተዋል።

25 ሺህ 039 ኪሎ ግራም ማዕድን ለማምረት እና 6 ሺህ 569 ዶላር ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ 32 ሺህ 153 ኪሎ ግራም ምርት እና ከ9 ሚሊየን በላይ ዶላር መገኘቱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የማዕድን ምርት ማደጉን እና በሀገር ውስጥ ምርትም 138 ሚሊየን ዶላር ገደማ የውጪ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።

ያለፈቃድ የሚሠሩ እና ሕገ ወጥ የማዕድን ማምረት ሥራን ለመከላከል መሠራቱን አንስተዋል።

ለማዕድን ፋብሪካዎች ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ምርታማነታቸውን ለማሳደግ መሠራቱንም ወይዘሮ አበባ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልሉ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል።
Next articleየክልሉን ኢኮኖሚ የሚደግፉ ውጤታማ ሥራዎች ተሠርቷል፡፡