
ባሕር ዳር: ሐምሌ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤት እና የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት አቅርበዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኃይሌ ብርሃን በየደረጃው ያሉትን ምክር ቤቶች የተጣለባቸውን የሕዝብ ውክልና ኅላፊነት እንዲወጡ ድጋፍ እና ክትትል ማድረጉን ተናግረዋል።
በ71 ተቋማት ላይ የመስክ ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ አፈፃፀማቸውን እንዲያዩ ግብረ መልሶች ተዘጋጅተው እንዲደርሳቸው የተላኩ መኾኑን ነው የገለጹት።
በበጀት ዓመቱ 12 ሕጎች ወጥተው በየደረጃው ላሉ ለሁሉም ምክር ቤቶች መላኩን አንስተዋል። የተለያዩ ሀገራዊ እና ክልላዊ ሁነቶችን የማስተባበር ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።
በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላትን አቅም ከማሳደግ አኳያ ለ361 አፈ ጉባኤዎች፣ የምክር ቤት ተመራጮች እና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሠጠቱን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ጽሕፈት ቤትን ዓመታዊ ሪፖርት ያቀረቡት የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ዳንኤል ደሳለኝ እንደገለጹት በዝግጅት ምዕራፍ የእቅድ ዝግጅት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።
በክልሉ ከ119 የምርጫ ክልሎች የመራጭ ተመራጭ መድረኮች ተካሂደዋል፤ በቡድን እና በተናጥል የቀረቡ 21 የሕዝብ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች መፍትሔ መሠጠቱን በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ደንቦችን በማሳተም ማሰራጨት እንደተቻለም ተናግረዋል። በየደረጃው ያሉትን የአሥተዳደር ጽሕፈት ቤቶች የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል። በተደረገው የመስክ ክትትል እና ድጋፍ መሠረትም ግብረ መልስ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ነው ያሉት።
ምቹ የሥራ አካባቢን በመፍጠር በኩልም የቢሮ ዕድሳት እና ግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል። ከሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ተቋማት ጋር በመተባበር የዲጅታል ቴክኖሎጂ አሠራርን እየተተገበረ እንደኾነም ነው ያመላከቱት።
ለተቋሙ የተመደበውን በጀት በአግባቡ መጠቀሙንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!