ሰላማችን የምንጠብቀው እኛው ነን።

13

ባሕርዳር:ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ማኅበረሰቡ የተሳተፈበት የወንጀል መከላከል ሥራ ውጤታማ ነው። ማኅበረሰብ በወንጀል መከላከል ላይ ንቁ እና ብቁ ተሳትፎ ሲያደርግ ወንጀሎች ይቀንሳሉ፣ ሰላምም ይመጣል።
በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ምክንያት በማድረግ በከተሞች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የማኅበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ሥራ እየተሠራ ነው።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጫጫ ክፍለ ከተማ የዶክተር ከበደ ሚካኤል ቀበሌ የብሎክ አደረጃጃት መሪ አስፋው ንጋቱ በቀጣና እና በብሎክ ተደራጅተው አካባቢያቸውን እየጠበቁ መኾናቸውን ገልጸዋል። “ሰላም እና ደኅንነቱ የራሴ ነው” በሚል ሁሉም ሰላም እና ደኅንነቱን እየጠበቀ ነው ብለዋል።
በቀጣና እና በብሎክ ተደራጅተው መጠበቅ ከመጀመራቸው አስቀድሞ ስርቆቶች፣ ዝርፊያዎች እና ቅሚያዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል። በምሽት ብቻ ሳይኾን በቀንም ቅሚያ እንደነበር ነው የተናገሩት።
በቀጣና እና በብሎክ ተደራጅተን መጠበቅ ከጀመርን ወዲህ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ቅሚያ ቆሟል ነው ያሉት። ጥበቃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ሕዝቡ የራሱን ሰላም ለማስከበር በንቃት እየተሳተፈ መኾኑን ተናግረዋል። በራስ አቅም መጠበቅ ከጀመርን ወዲህ እፎይታ አግኝተናል፣ በቀን እና በምሽት ያለ ስጋት እየተንቀሳቀስን ነው፣ ይህም የመጣው ሕዝቡ ለሰላሙ በሰጠው ትኩረት ነው ብለዋል።
የቀበሌው ፖሊሶች ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩም ተናግረዋል። ፖሊሶች ያለ መሰልቸት በየአካባቢው እየተዘዋወሩ ሕዝቡን እንደሚያበረቱም ገልጸዋል።
ለሰላም የሚሰጥ ዋጋ ከምንም የበለጠ ነው ብለዋል። በየትኛውም አካባቢ ያለው ማኅበረሰብ ሰላሙን ማረጋገጥ እንደሚገባው ተናግረዋል። የራሱን አካባቢ መጠበቅ ከቻለ ከውንብድና፣ ከስርቆት፣ ከእገታ እና ከዝርፊያ ራሱን መጠበቅ ይችላል ነው ያሉት።
የዶክተር ከበደ ቀበሌ የብሎክ አደረጃጀት መሪ ደበበ በቀለ ሁሉም ሰው የራሱን ሰላም ለመጠበቅ ተደራጅቶ እየጠበቀ ነው ብለዋል። የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም በተራ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል። በብሎክ ተደራጅተው መጠበቅ ከጀመሩ ጀምሮ ወንጀሎችን መከላከያ መቻላቸውን ገልጸዋል።
አካባቢያችንን በመጠበቃችን በነጻነት ሠርተን መግባት ችለናል ነው ያሉት። ያለ ስጋት ወጥተው እንደሚገቡም ተናግረዋል። የአካባቢያችን ሰላም የምንጠብቀው ራሳችን ነን፣ የእኛን ሰላም ማንም መጥቶ ሊጠብቅልን አይችልም ነው ያሉት።
እያንዱንዱ ሰው ሰላሙን የራሴ ብሎ እየጠበቀ መኾኑንም ተናግረዋል። ፖሊስ ከሕዝብ ጋር እየሠራው ያለው ሥራ የሚደነቅ መኾኑን ገልጸዋል። ተግባብተን በመሥራታችን ችግሮቻችንን ፈትተናል ነው ያሉት።
የክልሉ ሕዝብ በየአካባቢው ተደራጅቶ ሰላሙን መጠበቅ እንደሚገባው ተናግረዋል። ሁሉም ሰው ተደራጅቶ አካባቢውን መጠበቅ ከቻለ ሰላም እንደሚረጋገጥ ነው የገለጹት።
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የጫጫ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ዳምጠው ኀይሉ በክልሉ የጸጥታ ችግር ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰላም ሥራዎችን ከሕዝብ ጋር መሥራታቸውን ተናግረዋል። ሕዝብን መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራታችን ሰላማችን ጠብቀናል ብለዋል።
ሕዝቡ ለሰላም መጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። በክፍለ ከተማው ዝርፊያ፣ ስርቆት እና ቅሚያ እንዳይኖር በቀጣና እና በብሎክ በማደራጀት ሕዝቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ አድርገናል ነው ያሉት።
በክፍለ ከተማው የሚገኙ የቀበሌ ነዋሪዎች በቀጣና እና በብሎክ ተደራጅተው አካባቢያቸውን እየጠበቁ ነው፣ ፖሊስም ከሕዝቡ ጋር ኾኖ እየሠራ ነው ብለዋል። ኅብረተሰቡ አካባቢውን እየጠበቀ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን አሳልፎ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ፖሊስ ሕዝብን እያስተባበረ እና ከሕዝብ ጋር እየተቀናጀ ሰላሙን ማስከበር እንደሚገባው ነው የተናገሩት። ከሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ እና የችግሩ ገፈት ቀማሽ የመጀመሪያው ሕዝቡ መኾኑን በማስረዳት ለሰላም በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ነገር በሰላም እንደሚፈታም ተናግረዋል። ከሕዝብ ጋር በመሥራታችን ለውጥ አምጥተናል፣ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ጸጉረ ልውጥ ሲያይ እንደማያሳልፈውም ተናግረዋል። ይህ ተሞክሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች መስፋት አለበት ነው ያሉት።
በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ያሬድ አበበ ኅብረተሰቡ በራሱ ተሳትፎ የራሱን ሰላም የሚያረጋግጥበትን አሠራር ተከትለን እየሠራ ነው ብለዋል። የወንጀል መከላከል ሥራቸውን ሕዝብን መሠረት አድርገው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል።
አደረጃጀት ፈጥረን ኅብረተሰቡን የማሳተፍ ሥራ እንሠራለን ያሉት ኀላፊው ከእነዚህ ሥራዎች መካከል የገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤት ማደራጀት እና ኅብረተሰቡ ፖሊሳዊ እና የወንጀል መከላከል ሥራዎች ላይ አብሮ የሚያቅድበትን እና የሚሠራበትን ኸሐኔታ መፍጠር ነው ብለዋል።
በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን በማስተባበር እና በማስተሳሰር አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ከተሞች በብሎክ አደረጃጀት ወንጀልን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ በወንጀል መከላከል ሥራዎች ላይ ሲሳተፍ እና በፖሊስ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ ሲኾን ሰላምን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት። ከማኅበረሰቡ የሚደበቅ ወንጀል እና ወንጀለኛ አለመኖሩንም ተናግረዋል።
የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በተለያዩ ምክንያቶች ተጎድቶ መቆየቱንም ተናግረዋል። የወንጀል መከላከል ሥራዎችን ከሌሎች አስተሳሰቦች ጋር መቀየጥ እንደማይገባም ገልጸዋል።
ከማኅበረሰብ ጋር በተሠሩ የወንጀል መከላከል ሥራዎች መረን የለቀቁ የወንጀል ድርጊቶችን መቆጣጠር እንደተቻለም ተናግረዋል። ኅብረተሰቡ ወንጀለኞችን አሳልፎ እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።
ማኅበረሰቡን ሲያማርሩ የቆዩ የእገታ ወንጀሎችን ሆ! ብሎ በመነሳት እየተከላከለ ነው ያሉት ኀላፊው አሁንም ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ሥራዎች ይጠበቃሉ ነው ያሉት።
ከኅብረተሰቡ ጋር በተሠሩ ሥራዎች በርካታ ለውጦች መገኘታቸውንም ገልጸዋል። የወንጀል መከላከል ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይሠራል ነው ያሉት። ኅብረተሰቡ ራሱን በራሱ የመጠበቅ አቅሙ ከፍ እያለ እንዲሄድ እያስተባበሩ እና እየጠበቁ መሄድ ይገባል ብለዋል።
በማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት አርዓያ የሚኾኑ ከተሞች እንዳሉም ተናግረዋል።
ሰላም ከሁሉም እንደሚቀድም መረዳት ይገባል ያሉት ኀላፊው ለሰላም መስፈን እና መረጋገጥ የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅ መረዳት ያስፈልጋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ሰላሙ በእጁ ላይ ነው፣ ወንጀል በአካባቢው እንዳይኖር የሚፈልግ ሁሉ ከማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ፖሊስ ጋር በመቀናጀት መሥራት አለበት ብለዋል።
የፖሊስ የወንጀል መከላከል ሥራዎች በታገዙ ቁጥር የወንጀል ስጋት እየቀነሰ እንደሚሄድ ነው የተናገሩት። ወንጀልን ለመከላከል ምንም አይነት ምክንያት መፍጠር እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
ሰላም የተረጋገጠበት ክልል መፍጠር የሚቻለው ማኅበረሰቡ በባለቤትነት መሥራት ሲችል ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡን የሚያማርሩ ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው።
Next articleበክልሉ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችን የማጠናከር ሥራ ተሠርቷል።