በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየተሠራ ነው።

14

ደብረ ማርቆስ፡ ሐምሌ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባሶሊበን ወረዳ ልምጭም ቀበሌ ዞናዊ የ2017/18 የመኸር ምርት ዘመን የስንዴ ሰብል የኩታ ገጠም የዘር ማስጀመሪያ መርሐግብር ተካሂዷል ።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ስንዴ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ በኾነው ባሶሊበን ወረዳ ልምጭም ቀበሌ የአንድ ጀምበር ኩታ ገጠም የስንዴ ዘር ዞናዊ ማስጀመሪያ መርሐግብር ነው የተካሄደው።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ሀብታሙ አሕመድ በተያዘው 2017/18 የመኸር ምርት ዘመን ከ640 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በመኸር ምርት ዘመኑ የግብርና ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም አሠራር በስፋት ተግባራዊ እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት ተወካይ መምሪያ ኀላፊው።

በዞኑ በስንዴ ሰብል ከሚሸፈነው 212ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 168 ሺህ ሄክታር የሚኾነው በኩታ ገጠም የሚሸፈን መኾኑን አስረድተዋል ። ከዚህም ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሠብሠብ እየተሠራ ነው፡፡
ዞናዊ የአንድ ጀንበር የስንዴ ዘር ማስጀመሪያ በተካሄደበት ባሶሊበን ወረዳ ከ22ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ ሰብል ለመሸፈን እየተሠራ መኾኑን የገለጹት የባሶሊበን ወረዳ ግብርና ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ስሜነህ አሞኜ ናቸው። ከዚህም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሠበሠባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በምርት ዘመኑ በወረዳው በ134 ክላስተሮች በ14 ቀበሌዎች ስንዴን በኩታገጠም ለማልማት ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ኀላፊው በአንድ ጀንበር 15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም ስንዴ ዘር ለመሸፈን ጥረት ስለመደረጉ ጠቁመዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ሙሉቀን ቢያድግልኝ የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘርን ጨምሮ ኖራ እና ሌሎችንም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
በባሶሊበን፣ በደብረ ኤልያስ፣ በጎዛምን፣ በማቻከል እና ሌሎችም ወረዳዎች ስንዴን በኩታገጠም መዝራት መጀመሩ ምርትን በኩታ ገጠም የማምረት ሂደቱን ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱን አመላካች ነው ብለዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ዋና አማካሪ እና የዞኑ ደጋፊ መሪ ኃይለልዑል ተስፋ በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘር አምራች ዩኒየኖችን በማቋቋም ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል፡፡
የአፈር ለምነትን በመጠበቅ እና አስፈላጊውን ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።

ዋና አማካሪው በኩታገጠም ማምረት አርሶ አደሮች ልምድ እንዲጋሩ ከማድረግ ባሻገር ሜካናይዜሽንን በመጠቀም የምርት ጥራትን ከፍ ለማድረግ እና የምርት ብክነትን ለመቀነስ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በባሶሊበን ወረዳ የልምጭም ቀበሌ አርሶ አደሮች ስንዴን በኩታ ገጠም መዝራት ከእርሻ ሥራ ጀምሮ እስከ ሰብል ሥብሠባ ድረስ ተግባራትን በተመሳሳይ ወቅት ለመፈፀም ከማስቻሉ በተጨማሪ ተባይ እና አረምን በጊዜ በመከላከል ምርትን ለመሠብሠብ ምቹ ኹኔታን የሚፈጥር ስለመኾኑ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበበጀት ዓመቱ በወንጀል ጉዳይ የተመዘበረን ከ398 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥት ሃብት ማስመለስ ተችሏል።
Next articleሰላማችን የምንጠብቀው እኛው ነን።